Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የአንድ ሌባ ጀግንነት ለሲዳማ ህዝብ ክልልነት(እውነተኛ ታሪክ)
==========================
ከአቶቴ ወደ አሊቶ ሰፈር የተሳፈሩት ሁለት ወጣቶች "አሪፍ"የሚባል አለባበስ የለበሱና ሁለቱም ዘመናዊ የሆነ ስልክ ይዘዋል። እነዚህን ሁለት ወጣቶች ፣ አንድ ዕድሜው ወደ 21 ዓመት የሚጠጋ፣ ቁመቱ ረዘም የሚል፣ ትንሽ ወፈር የሚልና መልኩ ጠይም የሆነ ወጣት ከአቶቴ ጀምሮ ወጣቶቹ በተሳፈሩት ባስ ተሳፍሮ ስወርዱም ወርዶ ይከታተላቸዋል። ወጣቶቹን የሚከተላቸው ወጣት ስራው ሌብነት ነው። ሁለቱ ወጣቶች አሊቶ ሔዋኖ ት/ት ቤት ፊትለፊት ጫማ ለማስጠረግ ተስማሙ ፤ የሊስትሮው ጠረጴዛ/መቀመጫ ከጫማ አስተካካይ ውጭ ሌላ ሰው አልነበረውም። ወጣቶቹ መቀመጣቸውን የተረዳ በቅርብ ርቀት ሲከታተላቸው የነበረው ሌባው ወጣት ከአጠገባቸው መጥቶ ተቀመጠ። ወጣቶቹ እንደተቀመጡ በአሊቶ ሔዋኖ ት/ት ቤት ላይ የተሰቀለውን የጠብቡ አሊቶ ሔዋኖን ፎቶ እያዩ ጨዋታቸውን ስለ አሊቶ ጀብደኛነት ማውራት ጀመሩ። ወጣቶቹ ስለ አሊቶ ሲያወሩ ፣ ሌባው ወጣት ደግሞ እንዴት አድርጎ ቢሳካለት ሁለቱንም ስልክ ካልሆነ አንዱን ስልክ መውሰድ እንዳለበት እያሰበ ያወጣል ያወርዳል። ይሁንና እንደዋዛ የተጀመረው የሁለቱ ወጣቶች ውይይት እንደ መጀመሪያው አልቀጠለም። የአሊቶን ፎቶ በማየት የተጀመረው ንግግር ፣ ከአሊቶ ፎቶ ወደ አሊቶ ራዕይ ተሸጋግሮ የወጣቶቹ ንግግር በወኔ የተሞላ ስሆን እነሱ ምንም አልተረዱም። የወጣቶቹ በወኔ የተሞላው ንግግር ቀስ በቀስ ወደ ስሜት እና ቁጭት እየተቀየረ ስመጣ ሌባው ወጣት በትኩረት ይመለከታቸው ጀመረ። የወጣቶቹ ንግግር ከእነሱም አልፎ የሌሎችን ስሜት የሚቀሰቅስና የሚያስቆጭ ሆኔ። ወጣቶቹ ስለሚያነሱት ዓይነት ጉዳይ መስማት የማይፈልገው ወጣቱ ሌባ ፣ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖበት የወጣቶቹን ንግግር ያለፍላጎቱ/ያለፕሮግራሙ መስማት ጀመረ ፣ቀስበቀስም በወጣቶቹ ስሜታዊና በሚያስቆጩ ንግግር ያለፕሮግራሙ የመስረቅ ዕቅዱን ረሳው። በወጣቶቹ ስሜትን በሚነካ ንግግር ፣ ስሜታቸው ከተነካ ሰዎች ውስጥ የመጀመሪያው ሌባው ወጣት ነበር። የወጣቶቹ ንግግር ትኩረት ያደረገው:- ጎዳና ላይ ስለወደቁ ወገኖቻችን፣ በስሜ ልማት ስለተፈናቀሉ ወገኖቻችን እና እየተፈናቀሉ ስለሚገኙ ፣ በየወረዳው በችግጋርና በተለያየ ችግር ስለሚሰቃዩ ወገኖቻችን ስሆን በተለይ የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጉዳይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት የንግግራቸው አብይ/ዋና ጉዳይ ነበር። የወጣቱ ሌባ ትኩረትም ከሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሆነና የውይይቱ አንዱ አካል ለመሆን አንዳንድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመረ። ወጣቱ ሌባ ከወጣቶቹ ውይይት ውስጥ ስለ ክልል የመረጠበት ዋናው ምክንያት ጎዳና ላይ መውደቅ፣ በስሜ ልማት መፈናቀል ፣ በችግጋርና በተለያየ ችግር መሰቃየት ወጣቱ የኖረበትና እየኖረበት ያለ ህይወት ስለሆነ ለእርሱ አድስ የሆነው ክልል የሚባለው ነገር ነበር።
===================
የማያውቁትን ለማወቅ መጠየቅ የዕውቀት መጀመሪያ መሆኑን የተረዳው ሌባው ወጣት የማያውቀውን ለማወቅ እና የውይይቱ ህጋዊ አካል ለመሆን የተወሰኑ ጥያቄዎችን ጠየቀ:- ክልል ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ክልል በመሆን የሚገኙ ጥቅሞችስ(በፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ወዘተ) ምን እንደሆኑ እና የትኛው ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ክልል የመሆን ዕድል እንዳገኘ ወጣቱ ሌባ ወጣቶቹ እንዲያብራሩለት ጠየቀ። ወጣቶቹም የዕውቀታቸውን ያክል ለጥያቄው ሰፊ ማብራሪያ ሰጡት። ሌባው ወጣት የሁለቱን ወጣቶች ማብራርያ ካዳመጠ በኃላ ወጣቶቹን አመስግኖ እራሱን መውቀስ ጀመረ። እስከ ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ አለማወቁ ቆጨው። ለምን አይቆጨውም? ሲዳማን የመሰለ ታላቅ ህዝብ ህገመንግሥታዊ መብቱ ተረግጦ ፤ ባይቆጨው ነው የሚገርመው። በነገራችን ላይ ይሄ ሌባ ወጣት ወደ ሌብነት የገባው ወዶና ፈቅዶ አይደለም አማራጭ ሲያጣ ጊዜ ነው እንጅ። ነገሩ እንድ ነው ይህ የዛሬው የ21 ዓመት ወጣት ገና ዕድሜው የ12 ዓመት ልጅ እያለ በልማት ስም መሬታቸው እና ሙሉ ንብረታቸው በመንግስት ይወሰዳል። መሬታቸውና ንብረታቸው ከተወሰደ በኃላ እንደ አብዛኛዉ በኢትይጵያ መሬታቸው በልማት ስም እንደተወሰደ ገበሬ በአጠቃላይና፣ ከሀዋሳና ከተለያዩ ከሲዳማ ወረዳዎች መሬታቸውን በልማት ስም በመንግስት ተዘርፈው ጎዳና ላይ ከወደቁ ቤተሰቦች ውስጥ የዛሬው የ21 ዓመት ወጣቱ ሌባ ቤተሰብ አንዱ ነበር። ይህ ወጣት ወደ ሌብነት ስገባ ሌባ አልነበረም ጎዳና ላይ ከወጣ በኃላ ከሞት ለማምለጥ ስል ነው እንጅ። እውነት ስንቱ ይሁን በልማት ስም ከሀብት ንብረቱ ተፈናቅሎ በሚማርበት ዕድሜው ጎዳና ላይ ፣ ስለወገኑ በሚቆረቆርበት ዕድሜው ወንዱ ወንጀል ሰርቶ እስር ቤት ስገባ ፣ ሴቷ ህይወቷን ለመምራት ገላዋን ስትቸረችር/ሴተኛ አዳሪ ስትሆን የነዚህ ወጣቶች ወላጆች ጧሪ አጥተው በየመንገዱ ወድቀው ማየት እጅግ በጣም ልብ ይነካል። ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን እንመለስና ፤ ከላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ወጣቱ ሌባ የዛሬውን የመስረቅ ፕሮግራሙን ሰርዟል። ይልቁንስ የወጣቶቹን ስሜታዊ እና በምሬት የተሞላ ንግግር እየሰማ ስለ ጉዳዩ ማለትም የሲዳማ ህዝብ ክልል ስለመሆን በጥልቀት ለማወቅ እየጓጓ ወጣቶቹን በሙሉ ትኩረቱ መስማቱን ቀጠለ። የዚህ ሌባ በውይይቱ ውስጥ ያለው ድርሻ በዛ ቢባል መጠየቅ ነው፤ ምክንያቱም በሚማርበት ዕድሜው ጎዳና ላይ ፣ ተምሮ ተመራምሮ ስለ ወገኑ በሚቆረቆርበት እና አስተያየት በሚሰጥበት ዕድሜው እስር ቤት እና የዕለት ጉርሱን ስፈልግ እያሳለፈ ነው። ስለዚህ ምኑን የሚያውቀውን አስተያየት ይሰጣል?። በውይይቱ ውስጥ ድርሻው መጠየቅ ብቻ ሆነ። "መጠየቅ ሙሉ ሰው ያደርጋል" የሚል መርህ ይከተላል ሌባው ወጣት።
-----------------------
በዚህ መርህ መሠረት ሌባው ወጣት የመስረቅ ዕቅዱን ስላስረሳው ጉዳይ የመጨረሻ ጥያቄ ስሜታዊ የሆኑ ወጣቶችን ጠይቆ ከእርሱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ በልቡ ማሰላሰል ጀመረ። የሌባው የመጨረሻው ጥያቄ የሚከተለው ነበር:- ስሜታዊ ሆኖ "ማነው ለሲዳማ ህዝብ ክልል የከለከለው!?" የሚል ነበር። ሁለቱ ወጣቶችም በወጣቱ ጥያቄ ትንሽ ፈገግ ብለው ለሲዳማ ህዝብ ክልል የከለከለው ማን እንደሆነ የዕውቀታቸውን መጠን ያክል ለወጣቱ ግልፅ አድርገው ነገሩት። በነገራችን ላይ እስከ አሁን ሁለቱ ወጣቶች ከአጠገባቸው የተቀመጠውና ጥያቄ እየጠየቀ ስሜታቸውን በጣም የሚቆሰቁሰው ወጣት ሌባ መሆኑን በጭራሽ አያውቁትም። እንዴት ያውቁታል? ሌባን በማየት መለየት እንዴት ይቻላል የሀገራችን አብዛኛው ባለስልጣን ምን ሆነና። ግን በማየት መለየት አንችልም። ወደ ዋናው ሀሳብ እንመለስና ፣ ለወጣቱ ጥያቄ የወጣቶቹ ምን ብለው መለሱለት፣ ሌባው ወጣትስ ለሲዳማ ህዝብ መብት የምን መስዋዕትነት ከፈለ ፣ እኛስ ከሌባው ና ከታሪኩ ምን እንማራለን? የሚሉ ጥያቄዎችን በሚቀጥለው ክፍል ለማቅረብ እሞክራለሁ ኮኔክሽኑን(Connection) ካላጠፉት ። የወጣቶቹን ምላሽና ሌባው የወሰደውን እርምጃ መገመት ይቻላል...

ገቱ ግርማ