Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማን የማንነት ጥያቄ ለማፈን መሞከር አደጋ አለው!!!


ከተለያዩ የታሪክ ምንጮች እንደሚንረዳውና በአሁኑ ጊዜም እንደሚናየው ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ ጠቅለል ባለ መልኩ በሁለት መንገድ ይስተናገዳል። አንደኛው በትክክል በህገመንግሥታዊና ሠላማዊ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው በሌላ አማራጭ መንገዶች ነው። የመጀመርያው አማራጭ መንገድ የህዝብ ሠላማዊ ሰልፍ መውጣት ሲሆን ከዚህ የሚከተለው ደግሞ ህዝባዊ አመጽና እምብተኝነት ናቸው። ይህ የትኛውም ህዝብ ያልተመለሰለትና ያልተከበረለት መብቱን ለማስከበር የሚያደርገው ትግል ነው። እነዚህ አማራጮች ለአገር ሠላም፣ መረጋጋትና ዕድገት እንቅፋት ከመሆናቸውም ባሻገር ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያቶች ናቸው። 
ብዙውን ጊዜ እንደሚናየው መንግሥት የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ በህገመንግሥታዊ መንገድ ሳያስተናግድ ስቀር ህዝቡ እነዚህን አማራጮች ለመጠቀም ይገደዳል። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በአገራችን የተከሰተውን እንኳን ብንመለከት የሚድሮክ ኩባንያን ኮንትራት ማደስ ያስከተለው ቀውስ ቀላል አልነበረም። ህዝቡ በሠላማዊ መንገድ የኮንትራቱን መታደስ ተቃውሞታል። የተለያዩ አክትቭስቶችም ይህንን አስመመልክቶ በየሚዲያው ድምጻቸውን ከፍ አደርገው ተቃውመውታል። ሆኖም ግን ለህዝብ ተቃውሞ ደንታ የለለው መንግሥት የህዝቡን ጥያቄ ሰምቶ ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ መመለስ አልፈለገም። ህዝቡን በማሸማቀቅ፣ ከሥራ በማባረር፣ በማሰር፣ በማሰቃየት፣ በመግደል እንድሁም በመደብደብ ለተለያዩ የአካልና ለስነልቦና ችግሮች በመዳረግ ከፍተኛ ልምድ ያካበተው ህወኃት መራሹ የኢህአደግ አምባገነን መንግሥት የህዝቡን ችግር የሚሰማበት ጆሮም ሆነ ፍላጎት አልነበረውም። 
የህዝቡን እሮሮ ከምንም ሳይቆጥር የለመደውን ህገወጥ ድርጊት በመከተል ኮንትራቱን አደሰ። ይህንን ተከትሎ የህዝብ ቁጣ በማየሉ ህዝቡ እሮሮውን በሠላማዊ መንገድ ለመግለጽ ሠላማዊ ሰልፍ በመውጣት ብሞክርም ከምንግሥት በኩል ምላሽ አልተገኘም። ምክንያቱም በታሪክ የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ የሰው አካል ላይ ጉዳት ሳይደርስና ንብረት ሳይወድም የኢህአደግ መንግሥት ለህዝቡ ጥያቄ መልስ መመለስ አያውቅበትምና። በመሆኑም ቀስ በቀስ የህዝቡ ሠላማዊ ትግል ወደ ህዝባዊ አመጽ ተሸጋገረ። ይህን ተከትሎ የመንግሥት ወታደሮች ህዝቡ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ኢህአዴግ የፈለገው የሰው ህይወት ጠፋ፤ የሰው አካል ላይ ጉዳት ደረሰ፤ ንብረትም ወደመ። በሠላማዊ መንገድ በክብር ለህዝቡ ጥያቄ ጆሮ ሰጥቶ በህገመንግሥታዊ መንገድ ማስተናገድ ያልፈለገው ኢህአዴግ በህገወጥ መንገድ ያደሰውን ኮንትራት ሳይወድ በግድ ሠረዘው። እስክ ቆም ብለን እናስተውል ወገኖቼ። በመጀመርያ ለምን የህዝብ ጥያቄ በሠላም ሥርዓቱን ተከትሎ አልተስተናገደም? ለምንስ የንጹሓን ሰወች ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም አስፈለገ? በአገራችን ቀላሉን የህዝብ ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ ምላሽ ባለመስጠት ስንት ነፍስ እንደጠፋ፣ በስንት ሚሊዬን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመ እንድሁም ደግሞ ስንት ሰወች ለአካል ጉዳትና ለሥነልቦና ችግር እንደተዳረጉ መገመት አያቅትም።
ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት የማንነት ጥያቄን ህገመንገሥታዊ በሆነ መንገድ ስያቀርብ ኖሯል። የሲዳማን የማንንነት ጥያቄን ህወኃት መራሹ ኢህአዴግ መስማትም ሆነ መመለስ አይፈልግም። ይህንን ተከትሎ የዛሬ 16 ዓመት ግንቦት ወር ውስጥ ህዝቡ ሠላማዊ በሆነ መንገድ መብቱን ለማስከበርና ጥያቄውን ለማሠማት ያደረገውን ሠላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ብዙ ሰወች በኢአዴግ ወታደሮች ተገደሉ፤ ብዙወች በጥይት ተመተው እሮጠው የበቆሎ እርሻ በገቡበት እርዳታ ሳያገኙ መሽቶባቸው በጅብ ተበሉ፤ ብዙወቹም ለተለያየ የአካል ጉዳትና ለስነልቦና ቀውስ ተዳረጉ። 
ይሁንና ግን የኢህአዴግ መንግሥት የተከፈለው ዋጋ በቂ አይደለም ያለ ይመስል የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ ህዝቡን በተለያዩ ስልቶች ጸጥ አሰኘ። ህዝቡን የጨፈጨፉና ያስጨፈጨፉ ግለሰቦችን ወደ ህግ ፊት አቅርቦ ተገብውን ፍርድ ከመስጠት ይባስ ብሎ ይህንን ወንጀል ለፈጸሙና ላስፈጸሙ ግለሰቦች የሥልጣን እድገት ሰጣቸው። የሲዳማን ህዝብ በመጨፍጨፍ ሬዙሜያቸውን ያሳደጉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ክልል ተነስተው ወደ ፌደራል መንግሥት ተዛወሩ። ከ86ቱ አንዱ የሆነውን የሲዳማን ብሄር ህዝብ በመጨፍጨፍ ጥሩ ተሞክሮ በማሳየታቸው መላውን የኢዮጵያ ህዝብ መጨፍጨፍ የሚችሉበት ስልጣን ተሰጣቸው።
የተሰጣቸውንም ሥልጣን በከንቱ አላባከኑትም፤ ሌትተቀን ተግቶ በመሥራት በየቀኑ የኢትዮጵያን ህዝብ በመጨፍጨፍ ሥራ ላይ ተጠመዱ። ለዕድገትና ለልማት ገንዘብ የለላትን አገር ሰውን የሚከታተሉበትን ዘመናዊ ተክሎጂ ካደጉት አገር በመግዛትና በብዙ ሚሎዮን የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ ባለሙያወችን በማሰልጠን “ማን ምን አለ?፣ ማን ስለኛ ምን ጻፈ?፣ ማን ከማን ጋር አወራ? ወዘተ ” እያሉ በመሰለል ለብዙ ሺወች የሚቆጠሩ ንጹሓን ኢትዮጵያውያንን በማደን እስር ቤቶችን አጨናነቁ። በዓለም አቀፍ መንግሥታት የተወገዙትን ሰዉን ማሰቃያ መንገዶች በመጠቀም እሥረኞችን አሰቃዩ። ከዛም የተረፉትን በእሥር ቤት እያሉ በኢሳት አጋዩአቸው። 
ሆኖም ግን ይህን ተከትሎ የህዝቡ፣ በተለይ የወጣቱ ቁጣ ገንፍሎ በመዉጣቱ መቆጣጠር አቃታቸው። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገርቷ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ። አሁንም የህዝቡ ቁጣ ልበርድ አልቻለም። ህዝቡ ለዘመናት ስታለል ስለቆየ የኢህአደግን ስልት ሙሉ በሙሉ ተረድቶታል። ለዘመናት እንደጠላት እንድተታዩ አድርገው የለያዩአቸው የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች አንድነታቸውን በማጠናከር ቄሮና ፋኖ ብለው እራሳቸውን በመሰየም ትግሉን አቀጣጠሉ። አሁን ጉዳዩ ከቁጥጥራቸው ወጥቷል፤ የተለመደው የመግደል፣ የማሰር፣ የማሰቃየት፣ የማንገላታት፣ አስቸኳይ አዋጅ የማወጅ ብሎም በተለያዩ ስልቶች ማስፈራራት እየሠራ አይደለም። ለዘመናት አጋሮቻቸው የነበሩ አንዳንድ የውጭ አገራትም ቢጫ ካርድ ማሳየት ጀምረዋል። እንድ ነገር መደረግ ነበረበት፤ ብያንስ ብያንስ የአቅጣጫ ለውጥ ማድረግ የግድ ነበር። 
ይህ በእንድህ እንዳለ የኢህአዴግ አመራር ለሁለት ተከፈለ። አንደኛው ወገን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ከህዝቡ ጎን በመሆን ኢትዮጵያን ኣንድ አድርጎ የተከሰተውን ችግር ተነጋግሮ መፍታትንና የተለመደው የኢህአዴግ አሰራር የማያዋጣ መሆኑን የተረዳ(ቲም ለማና ገዱ)ሲሆን ሌላው ደግሞ የድሮውን የአፈናና የጭቆናን መንገድ እንደ ብቸኛ መንገድ የመረጠው ቡድን። የወጣቶቹን ቁርጠኝነት ያዩ የኦህዴድና የብአደን አመራሮች ከህዝቡ ጎን መሆን አማራጭ የለለው ማምለጫ መሆኑን ተገንዝበዋል። ህወኃት አደጋ ላይ ወደቀ። የህዝቡን አመጽ በየቦታው መቀጣጠልንና ከላይ የጠቀስኳቸው አመራሮችን የሃሳብ ለውጥ ያዩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሎቄው ስልት እንደማይሠራ በደንብ ተገንዝበዋል። በመሆኑም የሊቢያው መሪ የነበሩት የመሓመድ ጋዳፊ ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ሥልጣን በአስቸኳይ መልቀቅ ብቸኛው መፍትሔ መሆኑን በደንብ ተረዱ። 
በሌላ በኩል ደግሞ ህወኃት ብቻውን መቅረቱ ነው። በንደዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ እያሉ የሲዳማን ህዝብ በማፈን በህወኃት ስሸለም የኖረው ሌላኛው የደህዴን አባል አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ጌቶቹን መካድ አልፈለገም፤ እስክመጨረሻው አብሮአቸው ለመጓዝ የገባውን ቃል ኪዳን ማፍረስ አይፈልግምና። የሆነ ሆኖ የነለማ ቡድን በአሸናፈነት አልፎ ዶ/ር አብይ አህመድ ሥልጣን ይዘው አገርቱን በተወሰነ መልኩም ብሆን አረጋግተውታል።
ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስና ከላይ እንደጠቀስኩት የሲዳማ ህዝብ ለዘመናት በህገመንግሥታዊ መንገድ የማንነት ጥያቄን ስጠይቅ ኖሯል። ይህ የማንንት ጥያቄ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ምላሽ ሳያገኝ ስታፈን ቆይቷል። ይህ ጥያቄ ከታፈነበት ከእንደገና ተነስቶ በሠፍው እየተወራ ይገኛል። ይህ ጥያቄ ህገመንግሥታዊ ምላሽ በአስቸኳይ ካላገኘ የሲዳማ ህዝብ የተለመዱትን አማራጭ መንገዶች ለመጠቀም ይገደዳል። የመጀመርያው አማራጭ መንገድ ከላይ እንደጠቀስኩት ሠላማዊ ሠልፍ መውጣት ሲሆን ጥያቄው በዚህ የማይመለስ ከሆነ ግን ወደ ህዝባዊ አመጽ መሸጋገሩ የግድ እንደሚሆንና ያ ደግሞ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ለሰው ህይወት መጥፋት፣ ለሰው አካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ልሆን እንደሚችል የማይካድ ሃቅ ነው። ስለዚህ ይህ መሠረታዊ የሲዳማ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሌላ ደም ሳይፈስ፣ ንብረት ሳይወድምና፣ የአገራችን ዕድገት፣ ልማትና ሠላም አደጋ ላይ ሳይወድቅ አስቸኳይ ምላሽ ልሰጥበት ይገባል።
ድል ለጭቁኑ ለሲዳማ ህዝብ!!!