Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የፍቼ ጫንባላላ በዓል ምንነትና የአከባበር ሥነ ሥርዓት

የሲዳማ ብሄር በዓለም ላይ ካሉ ህዝቦች መካከል ጥቅት የራሳቸዉ ዘመን መለወጫ በዓል ካላቸዉ ህዝቦች የመጀመሪያዉ እንደሆነ የተለያዩ ጸሐፍ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ እኔም ዛሬ የፍቼ ጫንባላላ በዓል ምንነትና የአከባበር ሥነ ሥርዓቱን እንደሚከተለዉ ጃባ አልኩላችሁ፡፡
1. የፍቼ በዓል አከባበር
ፊቼ ጫንባላላ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ሰፋ ያለ ባህላዊና ማህበራዊ ትርጉም ያለዉ ነዉ፡፡ የፍቼ በዓል የአከባበር ሥነ ሥርዓት፣ አብረዉት የተቆራኙ ባህላዊ እሴቶችና እምነቶች እንድሁም ጫዎታዎች ያሉት ነዉ፡፡
1.1 የፊቼ በዓል አከባበር ዝግጅትና የቅድመ-ሁኔታዎች
የፊቼ በዓል የሚዉልበት ቀን አወሳሰንና እወጃ በተመለከተ የጎሳ መሪዎች እንደየጎሳዉ አጠራር ወማ፣ሞቴ፣ጋሮ ወይም ጌሎ እየተባሉ የሚጠሩ መሪዎች የፊቼን ዓመተ በዓል አዋጅ የሚያዉጁት ለሁለት ወራት ያህል እየጾሙና ጸሎት ካደረጉ < usura e'e> በኋላ ነዉ፡፡ ለምሳሌ የአዛዉንቶች ስብሰባ < songo> በማድረግ እርስ በርስ ይፈታተሻሉ፡፡ ያጠፋ ካለ የማንጻት ወይንም ንስሃ የማስገባት ስርዓት ያከናዉናሉ፡፡
የፍቼ ቀን ከሳምንቱ ቀናት ቃዋዶ እለት የሚዉል ሲሆን አያንቶዎች አመቺ የሚሆነዉ መልካም ቀን ሲያሰሉ ይቆያሉ፡፡ ሁሉም የሲዳማ ጎሳ በዉስጡ የተስማማበትን በዓሉ የሚከበርበትን ዕለት ለሌላዉ ጎሳ ያሳዉቃል፡፡ ይህም የሚከናወነዉ በምልከታ < lao> ሌሊት ነዉ፡፡ ከዚያም ሕዝቡ በዛ ብሎ በሚገኝባቸዉ ቦታ የጎሳ መሪዎች የፊቼ በዓል አከባበር ዝግጅትና ሥነ ሥርዓት በሚመለከት አዋጅ ያዉጃሉ፡፡ የሚታወጀዉ ሕዝቡ ወደ ባሕላዊ አደባባይ <gudumaale> ወጥቶ ትላልቅ እናቶች ( ቃሪቾ) እና የአገር ሽማግሌ ባለበት እንድያከብር ነዉ፡፡
ሌላዉ የፊቼ በዓል ቅድመ ዝግጅት የቄጣላ ነዉ፡፡ ይህም በሁለት ተከፍሎ የጅማሬ ቄጣላ <safote qeexaala> እንድሁም ተከታይ ቄጣላ <addicha qeexaala> ይባላል፡፡ የጅማሬ ቄጣላ አዛዉንትና <cimeeyye> አረጋዉያን <womma> አስቀድመዉ ፆም <usura> ስለሚገቡ ፊቼ ዘጠኝ ቀን ሲቀረዉ ጾም በሚፈቱበት ዕለት የጅማሬ ቄጣላ በመጨፈር በዕለቱ ኡሱራ(ፆም) ይፈታሉ፡፡ የአዲቻ ቄጣላ በአመዛኙ የወጣትና የጎልማሳ ወንዶች ቄጣላ ሲሆን በየአከባቢዉ ባሉ ባህላዊ ገበያዎች ዉስጥ ለፊቼ አራት ቀን እስኪቀራቸዉ ድረስ ይጨፍራሉ፡፡ ከዚህ የቄጣላና የፊቼ ዓመት በዓል ቀን ዉሳኔና እወጃ በኋላ የሚቀጥለዉ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ነዉ፡፡

1.2 የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት
የፊቼ በዓል የሚጀመረዉ አመሻሽ ላይ ሲሆን ሥርዓቱም ፊጣራ < fiixaara> ይባላል፡፡ በፊጣራ እለትም እያንዳንዱ አባወራ እቤቱ ደጃፍ መሿለኪያ <hulluuqa> በማቆም በሁለት በኩል እሳት እንድነዲና በመሀከሉ አረንጓዴ ሳር ተደርጎ ቤተሰቡና የቤት እንስሶች በዚያ በኩል እንድሾልኩ ያደርጋል፡፡ የመሿለኪያዉ ትርሙ ከዓመት ዓመት የመሸጋገር ምልክት ሲሆን የሁለቱም እሳት ትርጉም ከአሮጌዉ ወደ አዲሱ ዘመን አለፍን እንደማለት ነዉ፡፡ አረንጓዴዉ ሣር የጥሩ ዘመን ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ለፊጣራ የሚቀርበዉ ማዕድ በቅቤ የራሰ ቆጮ <buurisame> በትልቅ ጎድጓዳ በሆነ የሸክላ ዕቃ <shaafeeta> ከወተት ጋር ነዉ፡፡ ይህም የሚበላዉ በዕድሜ ወይም በባሕላዊዉ እርከን ቅድሚያ የሚሰጠዉ ሰዉ ቤት ተኪዶ እዚያም ከተዘጋጀዉ ሻፌታ ጫፍ ላይ በቅቤ የራሰዉን ቆጮ ቆንጥሮ ‘ፍቼ ከዓመት ዓመት አድርሺን < fichee dirunni diro iillishinke> እያለ ወደተለያዩ አቅጣጫ በመበተን ከተባረከ በኋላ ነዉ፡፡ ይህም በታላቅ ቤት የመብላት ሥርዓት መጀመር < safo> ይባላል፡፡ ሽማግሌዎች ምግብ ዘግነዉ መበተናቸዉ መሬትን ‹ይህ ጥሩ ነገር ካንቺ የተገኘ ስለሆነ ከአንቺ ዘንድ ይቆይልን› እንደ ማለት ነዉ፡፡ በዚህም ሁኔታ የፊቼ በዓል ከቤት ቤት በመሄድ በጋራ የመብላት ሥርዓት ይጀመራል፡፡
የፊቼ በዓል ሁለተኛዉ ቀን ጫንባላላ <cambalaalla> ይባላል፡፡ የጫንባላላ አከባበር የሚጀመረዉ ንጋት ላይ ሲሆን ጧት አንገቱ ባልተሰበረ የሸክላ ዉሃ መያዣ ዕቃ <shaaqqo> የሞቀ ዉሃ ይመጣና ልጆች ፊታቸዉን ታጥበዉ ቅቤ ይቀባሉ፡፡ ከዓመት ዓመት አድርሰን ብለዉ ወደ ጎረበት የበዓሉን ድግስ ለመብላት ይሄዳሉ፡፡ በየደረሱበት ‹ቤቶች እንኳን አደረሳችሁ› <Ayidde cambalaalla> ሲሉ ተቀባዮቹም ‹ድረሱ ድረሱ› <iille iille> በማለት እያስተናገዱአቸዉ ሰፈር እየዞሩ ይመገባሉ፡፡
ከጫንባላላ ቀጥሎ የሚመጣዉ የፊቼ በዓል አከባበር ሂደት ሻሺጋ ‹shaashiga> ይባላል፡፡ ይህም የሚከበረዉ በገበያ ቦታዎች ወይም በባህላዊ አደባባዮች ‹Ggudumaale› ነዉ፡፡ ይህም በባህላዊ ጭፈራዎችና በፈረስ ጉግስ ደምቆ የሚከበር ሲሆን በተለይም ያላገቡ ወጣቶች ፍቅረኛ ለመያዝ ከፈለጉ የመተዋወቂያ ወቅት ነዉ፡፡ በ ‹ሻሺጋ› መገባደጃ በተለምዶ መፋቂያ ‹fiqiiqicho› ተብሎ በሚታወቅ የመልዕክት ልዉዉጥ ወጣቶቹ ወዳጅነት ለመመስረት ይችላሉ፡፡ የሻሺጋ መደምደሚያ የፊቼ መዉጣት ‹fichi-fulo› ቄጣላ የሚደረግ ሰሆን በዚህም ወቅት ህብረተሰቡ በየጎሳዉና በየጉዱማለዉ የሚጨፍርበት የፊቼ በዓል ማጠቃለያ ነዉ፡፡በዚህ ወቅት ተሞሽረዉ የቆዩ ሴቶች አምረዉና በአማቶቻቸዉና በጎረቤቶቻቸዉ ታጅበዉ ወደ አደባባይ የሚወጡበትና ሙሽርነታቸዉ የሚያበቃበት ነዉ፡፡ ማጠቃለያዉም የሚከናወነዉ በጎሳዉ ባህላዊ አደባባይ ከፍ ባለ ቦታ ላይ አዛዉንቶች የሀገር ሽማግሌዎች ለማሳረጊያ በሚሰጡት ቡራኬ ነዉ፡፡ ፊጣራ፣የጫንባላላና የሻሽጋ ዝግጅት በዉስጡ የተለያዩ ክንዋኔዎች ያሉት ነዉ፡፡ ይህም ለየት ካለ የምግብ አዘገጃጀት ጀምሮ የአመጋገብ ሥርዓትን፣የጭፈራና የተለያዩ ባሕላዊ የመግባቢያና የተሳትፎ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸዉ ናቸዉ፡፡
1.3 የፊቼ በዓል ባህላዊ እሴቶችና እምነቶች
በብሔሩ ከፊቼ በዓል የተቆራኙ ባህላዊ እሴቶችና እምነቶች አሉ፡፡ እነዚህም የተጣሉትን የማስታቅ፣ ለልጆችና ለቤት እንስሳትና ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ማድረግ፣አብሮ የመብላትና የመጠጣት ባሀል ናቸዉ፡፡ የተጣሉትን የማስታረቅ ጉዳይ የሚጀምረዉ ገና ለበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ ነዉ፡፡ የተጣላ ሰዉ መኖሩ ሲታወቅ ሽማግሌ ወጥቶ በመሀከላቸዉ ዕርቅ እንድወርድ ይጠይቃል፡፡ 
የተጣሉት ከዚህ በፍት የነበረዉን ነገር እንድረሱ በመጠየቅ ሰላምና ዕርቅ እንድወርድ ያደርጋል፡፡ ዕርቅ ካለወረዱ ተጣልቶ ያለ ሰዉ ፊቼን ለማክበር ይቸገራል፡፡ 
የጫንባላላ ዕለት ለልጆች ብቻ ሳይሆን ያለዉ ለሌለዉ የሚያስብበትና የሚያበላበት ዕለት ነዉ፡፡ በዚያን ዕለት ልጆች ይከበራሉ፣ በነሱ ላይ ኃይለ ቃል መናገር የተከለከለ ነዉ፡፡ በዚያን ቀን ልጆች ሥራ አይሰሩም፣የእነርሱን ሥራ የሚሰሩት አዋቂዎች ናቸዉ፡፡
ለቤት እንስሳትና ለተፈጥሮ የሚደረግ እንክብካቤን በሚመለከት ከብቶች በለመለመ መስክ ዉስጥ ይለቀቃሉ፣የማንም ይዞታ ቢሆን አይከለከሉም፡፡ በአድሱ ዓመት ጨዋማ አፈር ወይም ‹‹ ቦሌ›› ይሰጣቸዋል፡፡ በአዋቂዎች ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከብት በዚህ ቀን አይታረድም፤ በሥጋ አይደገስም፣ ሥጋ ቤት አያድርም፡፡
1.4 የፊቼ በዓል ዘፈኖችና ጨዋታዎች
በፊቼ በዓል ከሚዘፈኑ ዘፈኖችና ጨዋታዎች ዋና ዋናዎቹ ቄጣላ ‹qeexaala> ሆሬ <hore> እንድሁም ፋሮ ‹faaro› ናቸዉ፡፡ ቄጣላ የሚዘፈነዉ በወጣት ወንዶች፣በጎልማሶችና በአዛዉንቶች ነዉ፡፡ በፊቼ በዓል የቄጣላ ዘፈን በይበልጥ የሚያተኩረዉ የዉዳሴና የተቃዉሞ ስሜቶችን በማንጸባረቅ ላይ ነዉ፡፡ ይህም ለምሳሌ የፊቼ አደባባይና የፊቼ ዓመት በዓል ‹gudumaale› የሚሞገሱበት፣ እንድሁም የራስ ጎሳ ወይም የጎሳ እንድሁም የሀገር መሪ የሚወደሱበት ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቄጣላ ከጦርነትና ከጀግንነት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ተቃዉሞዎች ፣ የተለያዩ ጥያቄዎች የሚንጸባረቁበት የጋራ ስሜቶች የሚገለጹበት ነዉ፡፡
ሆሬና ፋሮ የወጣቶች ጭፈራዎች ናቸዉ፡፡ ሆሬ ‹hore› የልጃገረዶች ዘፈን ወይም ጨዋታ ሲሆን ልጃገረዶች ያሉበት የልጃገረድነት ጊዜና ዉበታቸዉን ማሞገስ እርስ በርስ መሞጋገስና መጎነታተል አቻ ወጣት ወንዶችን ለመሳብ የሚሰነዘር አባባሎችንና የሚወዱአቸዉን ወጣት ወንዶች የሚያወድሱ መልዕክቶችን ያካትታል፡፡ ፋሮ ‹faro› ያላገቡ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የሚጫወቱት ጭፈራ ሲሆን ዘፈኑን በግጥም ‹kiiro/maammaashsha› የሚሰነዝሩት ወንዶች ናቸዉ፡፡ በዚህም ወንዶቹ የሚፈቅዱአቸዉን የማወደስ አልያም የሚጎነትል ራስንና ባልደረባን የሚያሞግስ በህብረተሰቡ ዉስጥ የሚታዩ ልዩ ልዩ ተግባራትን የሚያሞግስ፣የሚተች ወይንም የሚጠይቅ ነዉ፡፡
ከጫንባላላ ዕለት በኋላ ቢያንስ ለሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ትላልቅ ወንዶች ለቄጣላ ይወጣሉ፡፡ የሚጨፍሩት ፀጉራቸዉን አበጥረዉ፣ጥሩ ለብሰዉ፣ ቅቤ ተቀብተዉና የተለየ የቄጣላ ዓይነቶችንና ቅደም ተከተሎችን ይዘዉ ነዉ፡፡ በዚያን ጊዜ የተለያዩ ዉዳሴዎች፣ቅሬታዎች ወይም ዉዳሴዎች ይገልጻሉ፡፡ በጭፈራዉ ወቅት መሪዎች ይወደሱበታል ወይም ይነቀፉበታል፡፡ ልጃገረዶች ‹ሆሬ› የተባለን የተናጠል ጫወታና ‹ፋሮ› የሚባለዉን ጨዋታ ከወጣት ወንዶች ጋር ይጫወታሉ፡፡ በዚህም አጋጣም እርስ በእርስ መተዋወቂያ መድረክ ያገኛሉ፡፡
ወድ አንባቢዎቼ ለዛሬ ያለኝን እዚሁ አበቃሁ በቀጣይ በተመሳሳይ ወይንም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ እስከሚንገናኝ ደህና ሁኑ፡፡ 

Ayidde cambalaalla!!!!!!!! 
አይዴ ጫንባላላ!!!