Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ማቴዎስ ኮርስሳ ለምን ተገደለ?(በቤታና ሆጠሶ)  

በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ብሄረሰቦች ዜግነታቸው ተክዶ፤ ኢትዮጵያዊ እኛ ብቻ ነን በሚሉ ግብዞች፣ ስለመብቱ ባነሳቸው ጥያቄዎች በግፍ የተጨፈጨፈበት በአንጻሩም ኢትዮጵያዊነት የተሸረሸረበት ወቅት መኖሩ የማይካድና ብዙዎቻችን የምናውቀው ሐቅ ይመስለኛል። ህዝብ ሳይወክላቸው በዝምድና፤ በጋብቻ አምቻ፤ በአንድ አካባቢ ልጅነት ተመራርጠው በህዝቡ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ እንደቆዩም ይታወሳል። 
   
    እነዚህ ባለሥልጣኖች እንደጅብ ወይም እንደተኩላ ተጠራርተው የሲዳማን ኢኮኖሚ እንዴት እንደተቀራመቱት ስገልጽ ትኩረቴን በአለታ ወንዶ ላይ ያደረኩት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ለምን ቢባል በወቅቱ ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት የነበረውና በአንፃሩም ከሁሉም ይበልጥ መጠነ-ሰፊ ብዝበዛ የተካሄደበት ሕዝብ ይህ በመሆኑ ነው። ይህም ሲባል መጠኑ ይበላለጥ እንጂ እንደ ቆዳ የተገፈፈው የሲዳማ ሕዝብ በጠቅላላው መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የተበደለው የክፍለ ሀገሩ ጠቅላለው ህዝብ ቢሆንም፣ የቡና አካባቢ ተብለው ይበልጥ የተዘረፉት የሲዳማና የጌዲኦ ሕዝብ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ በወቅቱ የእነዚህ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን በሥርዓቱ አንካፈልም በማለታቸው ለሕዝባቸው የሚከራከሩ ወገናዊነት የሚሰማቸው ተቆርቋሪ የሆኑ ምሁራን በሌሉበት፣ ተቆርቋሪ የሆኑ የገበሬ ተወካዮች እንኳ በመኻከላቸው ቢገኙ ሕይወታቸውን እስከማጣት የደረሱ እንደነበርም ታውቋል፡፡ ለዚህም ምሳሌ ቢያስፈልግ የማቴዎስ ኮርስሳን ግድያ መጥቀሱ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል ብዬ ስለአመንኩና በደርግ ዘመን የነበረውን የፍትህ ሥርዓት ገጽታ ይገልጻል ብዬ ስለገመትኩኝ ታሪኩን ከሞላ ጐደል ከዚህ በታች አቅርቤአለሁና ተመልከት።

   ማቴዎስን ለሞት ያበቃው የፖለቲካ አመለካከት (ideology) ልዩነት ሳይሆን ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ መሆኑን ቀደም ብዬ በሌላው ክፍል ጠቅሻለሁ፡፡ ማቴዎስ በጣም ረጋ ያለና ጭምት ሰው ሲሆን፣ ደርግ በነበረው መዋቅር ውስጥ በፍጥነት አሳድጐት እንደነበር በሌላው ክፍል አስረድቼአለሁ፡፡ ዳሩ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ከፍተኛ ቦታ በመድረሱ ምናልባትም ብዙዎች ሌሎች እንደ አደረጉት፣ ሹመቴ ይነካብኛል ብሎ ከሕዝቡ አልራቀም (ሕዝቡን አልከዳም)፡፡ ይልቁንም ለሕዝብ የቆመና ወገናዊነት የሚሰማው ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም ከሌባና ቀማኛ ባለሥልጣናት ጋር ሊስማማ አልቻለም፡፡ ማቴዎስ በልማት ስም ተዋጥቶ ይዘረፍ በነበረው ገንዘብ ሁኔታ በጣም ያዝን ነበርና በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ በግልጽ ያወግዝ ነበር፡፡ በመሆኑም ጥላቻቸውም ግልጽ መሆን የጀመረው በወቅቱ የክፍለ-ሀገሩ አስተዳዳሪ ተፈራ እንዳለው(ቅጽል ስሙ ጉቦ ተፈራ) የሕዝብ አዳራሽ አስሠራለሁ ብሎ በልማት ስም በሰበሰበው ገንዘብ ላይ ነበር፡፡ ያህንን ገንዘብ ያዋጣው የክፍለ ሀገሩ ሕዝብ በሙሉ ቢሆንም ይበልጥ የተጐዳውና አብዛኛውን ገንዘብ ያዋጣው ግን የሲዳማ ገበሬ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ያንን ገንዘብ ሲያዋጡ ከብት ያላቸው ገበሬዎች ከብቶቻቸውን (የእርሻ በሬ ሳይቀር) ሽጠው ሲከፍሉ፣ ከብት የሌላቸው ግን የሚለብሱትን ልብስ፣ እንደ ብርድልብስ ያለ (ቡልኮ) ሳይቀር ሽጠው እንደከፈሉም ታውቋል፡፡ በዚህ መዋጮ የሚበላውና የሚለብሰው የሌለው ገበሬ ተገዶ ልማት በሚል ማስፈራሪያ በሚያዋጣው መዋጮ፣  የሚጠቅሙት መስለው ደሙን እንደመጠጡት ልብ ያለው አንባቢ አስከፊነቱን ሊረዳ ይችላል ብዬ አምናለሁ። 

ያም ሆነ ይህ በዚህ መልክ ለአዳራሽ ሥራ ተብሎ የተሰበሰበው ገንዘብ አሥራ-ሶስት ሚሊዮን ብር እንደነበርም ተረጋግጦአል፡፡ ያ ሁሉ ገንዘብ  ለአዳራሹ ሥራ ወጪ ሆኖአል ተብሎአል፡፡ ታዛቢዎች ግን አዳራሹ ቢበዛ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ አይጨርስም ብለው ይገምታሉ (አንባቢያን የብሩን ዋጋ በዛሬው ሳይሆን በዚያን ጊዜ በነበረው እንዲያስቡት ያስፈልጋል)፡፡ ማቴዎስ ኮርስሳ ያንን ገንዘብ ኦዲት ለማስደረግ ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቶአል፡፡ ይህ ነበር በአቶ ተፈራ እንዳለና ማቴዎስ መካከል ከፍተኛ ቅራኔ የፈጠረው፡፡ በመሆኑም ያ ቅራኔ እየሰፋ ሄደ እንጂ ጋብ ያለበት ጊዜ አልነበርም፡፡ ኦዲቱ እንዳይሳካ ያደረጉት ደግሞ ከላይ ሆነው ለዋና አስተዳዳሪው ሽፋን የሚሰጡትና ከሕዝብ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ከእርሱ ጋር የሚቀራመቱት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንደነበሩም በግልጽ ይታወቅ ነበር፡፡ ለእነዚያ ባለሥልጣናት ከሲዳማ ተዘርፎ የሚሄድላቸው፣ ጥሬ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ቅቤ፣ማር (ነጭ ማር ከሀገረሳላም፣ ከሆሮሬሣና ከቦሬ)፣ ጤፍ ከባንሣ ሲሆን፣ በጣም የሚያስገርመው ግን በአዲስ አበባ ሥጋ ሳይጠፋ በአለታ ወንዶ ከሚታረደው ሉካንዳ ምርጥ የሆነ ሥጋ እየተመረጠ በገበሬ ማሕበር መኪናዎች ተጭኖ እስከ አዲስ አበባ ድረስ በተፈራ እንዳለው አማካኝነት ይላክ እንደነበርም ታውቋል፡፡ ስለሆነም ባለሉካንዳዎች ሌሊት ተነስተው ምርጥ በሬዎችን እንዲያርዱ ተነግሮአቸው ያድሩና ጧት ተነስተው ሲያርዱ ሥጋው ወዲያውኑ በገበሬዎች መኪና ተጭኖ አዲስ አበባ ላሉት ባለሥልጣናት ትኩስ ሥጋ ለምሳ እንደሚያደርሱ የገበሬ ሾፌሮች ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሚጫነው አብዛኛው ሥጋና ማር የሚሄደው በወቅቱ የአገር አስተዳዳር ሚኒስቴር ለነበረው ለእንዳለ ተሰማ ሲሆን፡ ለሌሎቹም በእርሱ አማካይነት እንደሚደርሳቸው ታውቋል፡፡ ይህን ንብረት አብዛኛውን ከእንዳለ ተሰማ ጋር የሚካፈለው የቁንጮው ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሰሐ ደስታ መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህንን ይበልጥ ለመረዳት የሚፈልጉ ካሉ፣ በዚያን ዘመን የአለታ ገበሬዎችን መኪና ሲነዱ የነበሩ ሾፌሮች፣ በግልጽ የሚያስረዱ ስለሆነ አሁንም በሕይወት አሉና ይጠይቁ፡፡ ቁም ነገሩ ግን በዚህ መልክ ነበር የሲዳማን ሕዝብ ደሙን (ወዙን) መጥጠው፣ሥጋውን ገሽልጠው አጥንቱን ብቻ ያስቀሩት።
   
   የማቴዎስና የክፍለ ሀገሩ ዋና አስተዳዳሪው ተፈራ እንዳለው (የደርግ መንግሥት ወድቆ ሸሽቶ ሲሄድ በጉቦ ከሰበሰበው ሌላ ከአዋሣ ባንክ የሚበቃውን ያህል ገንዘብ ዘርፎ የሄደ በመሆኑ ዛሬ በኬንያ ውስጥ የተደላደለ ኑሮ ይኖራል) የሁለቱን ቅራኔ በጣም አስከፊ  ደረጃ የደረሰው ዋና አስተዳዳሪው “ለሀገረሰላም ከተማ መብራት አስገባለሁ” በሚል ሰበብ፣ በተለመደው ልማት ስም ገንዘብ ሰብስቦ ለመብላት ፈልጐ ሕዝቡ ገንዘብ መዋጮ እንዲያደርግ ትዕዘዝ ሲሰጥ ነው፡፡ ከዚህ ከሚዋጠው ገንዘብ ስድስት መቶ ሺህ ብር የገበሬው ድርሻ ሆኖ፣ ገበሬው በፍጥነት እንዲያዋጣ በዋና አስተዳዳሪው ደብዳቤ ታዛዘ፡፡ ማትዎስ ግን ከዚያ በፊት በአዳራሹ ስም የተበዘበዘው ገንዘብ ሲያሳስበው የቆየ ከመሆኑም በላይ “ገበሬው ያለአግባብ ሲበዘበዝ ለምን ዝም ብላችሁ ትመለከታላችሁ?” የሚል ግፊት ከየአቅጣጫው ይደርሰው ስለነበር፣ በዚህ ዓይነት ሌላ እንደገና እንዲደገም አልፈለገም፡፡ በመሆኑም፣ የክፍለ ሀገሩ የገበሬዎች ማሕበር ሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ ሰብሰቦ “ከእንግዲህ ወዲህ የክፍለ-ሀገሩን የገበሬዎች ማሕበር ሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ አይቶና፣ አምኖ ካላፀደቀ በስተቀር ማንኛውንም ዓይነት መዋጮ ገበሬ ሊያዋጣ አይችልም” የሚል ውሳኔ አስወስኖ፣ ደብዳቤውን ወዲያውኑ በገበሬዎች መካከል አሠራጨ ፡፡ በዚህ ጊዜ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ተወጥሮ የነበረው የሀገረሰላም ገበሬ ይህንን ሲሰማ በደስታ ፈነደቀ፡፡ በተቃራኒው ግን ዋና አስተዳዳሪው በጣም ተናደደ፡፡ በመሆኑም ለማትዎስ ስልክ ደውሎ “የሀገረሰላም ገበሬ የልማት መዋጮ እንዳያደርግ የከለከልከው አንተ ነህ ወይ?” ብሎ ሲጠይቀው፡ ማቴዎስ ምንም ሳያወላወል “አዎን” ብሎ መለሰለት፡፡ “ለምን” ብሎ ሲጠይቀው፣ “አስፈላጊ ስላልሆነ ነው” የሚል መልስ ሰጠው፡፡ በዚህ ጊዜ ሰውዬው በጣም ተናደደና “ልማት አይሠራ ነው ወይ የምትለው?” ብሎ ሲጠይቀው፣ ማቴዎስ የሰጠው መልስ “ለጕሮሮው የሚበላው የሌለው ገበሬ ለከተማ ልማት መዋጮ ለማድረግ አይችልም፣ አቅምም የለውም” ብሎ ሲመልስለት፣ ሰውዬው በጣም ተቆጣና “የልማት እንቅፋት ለምን ትሆናለህ?” ብሎ ሊያስፈራራው ቢሞክርም፣ ማቴዎስ ግን በአቋሙ ጸና፡፡ “ለራሱ የሚበላው የሌለው ሕዝብ፣ ቤተሰቡ እየተራበ ሳለ፣ ከራሱ ልማት አልፎ ሌላውን ለማልማት መዋጮ ሊያደርግ አይችልም፣ ማድረግም አይገባውም ብያለሁ፣ ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር የለም” አለው፡፡ ተፈራም በጣም ተናደደ፡፡ ከዚያም ለአለቆቹ በተለይም በጊዜው አገር አስተዳደር ሚኒስትር ለነበረው ለእንዳለው ተሰማ ስልክ ደውሎ ምክር ይጠይቃል። “ማቴዎስ በጣም አስቸገረኝ፣ ጕሮሮአችንን ዘጋ፣ የጐሮሮ አጥንት ሆነብን፣ ምን ማድረግ ይሸለኛል?” ብሎ ሲያማክረው፣ ለዚህ እንዳለው ሲመልስለት፣ “አንተ ምን ነካህ አንድ ጣት (በወቅቱ በሥልጣን አካባቢ የነበረው ሲዳማ ማትዎስ ብቻ ስለነበር አንድ ጣት ተብሎአል) ቆርጦ መጣል ያቅተሃል ወይ? ይህን ያህል ሥልጣን ይዘህ ተቸገርኩ ትላለህ? ገለል አድርገው እንጂ” ይለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ተፈራ በጣም ደስ አለውና ሰውዬው የተናገረውን እንዲያረጋግጥለት ፈልጐ፣ እንዲህ አልክ ወይ? ብሎ እንደገና ሲጠይቀው፣ አለቃው መለሰና እንግዲህ ምን ብዬ ልንገርህ? ይህ ሁሉ ያንተ ድክመት ነው ብሎ ገስፆታል፡፡ 

ስለሆነም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነበር ተፈራ ማቴዎስን ለማጥፋት (ገለል ለማድረግ) ዘዴ መፈለግ የጀመረው። በመሆኑም ማቴዎስ የሚገባበትን ቦታና የሚሄድበትን አቅጣጫ በስውር ማጥናት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሲከታተል፣ ማቴዎስ የሚያመሽበት ቤት በሐዋሣ ከተማ ውስጥ መጠጥ ቤት ያላትና ማቴዎስ በወዳጅነት የያዛት አንዲት ሴት መኖሩዋን ተረዳ፡፡ ያንን ወጥመድ አዘጋጅቶ የማትዎስን አካሄድ በስውር ሲከታተል ሳለ፣ ማቴዎስ ለሥራ ጉዳይ ከሌሎቹ ጋር በቡድን ሆኖ ወደ መስክ (ፊልድ) ወጡ፡፡ ከመስክ ወጥቶ ማቴዎስ የት እንደዋለና የት እንደአደረ አጥብቆ ይከታተል ነበር ተፈራ። ያንን ያልተረዳው ማቴዎስ ከቡድኑ ጋር በመሆን፣ ከጌዲኦ አውራጃ ጀምረው በየወረዳዎቹ ሲዞሩ ከርመው ወደ ዳሌ ደረሱና ማደሪያቸው በይርጋዓለም ከተማ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ማትዎስ ቤቴ እዝህ ቅርብ ሆኖ ሳለ እኔ እንዴት በከተማ አድራለሁ ሂጄ በቤቴ ልደር ብሎ ቡድኑን ሲያማክራቸው፣ እነርሱም ለጧት ሥራ በጊዜው ድረስ እንጂ አሁን ሄደህ በቤትህ ልታድር ትችላለህ ስለአሉት፣ ማትዎስ ሾፌሩን ጠርቶ ወደ ቤቴ አድርሰኝ አለው፣ ሌሎቹም የቡድኑ አባላት እርሱን (ማቴዎስን) ይዘህ ስትሄድ እግራ-መንገድህ እኛንም ደግሞ ወደ ፍልውኃ አድርስንና እርሱን አድርሰህ እስክትመለስ ድረስ ተጣጥበን ስለምንጠብቅህ ይዘኸን ትመለሳለህ ብለው ነገሩት። ሁሉም በዚህ ተስማምተው ማቴዎስን ወደ ቤቱ ይዞት ሲሄድ፣ የሥራ ባልደረቦቹን በፍል-ውኃ አውርዶአቸው ሄደ፡፡ እዚህ ላይ የቡድኑ አባላት የነበሩት 1ኛ መንግሥቱ ሸዋዬ የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ኢሠፓ ኦዲት ኮሚሽን ኃላፍ፣ 2ኛ ወርቁ ሀንቃ የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ገበሬዎች ማህበር የኦዲት ኮሚሽን ተጠሪ  ነበሩ፡፡ እንግዲህ ሾፌሩ ማትዎስን ወደ ቤቱ አድርሶ ሲመለስ እነ ወርቁን ከፍልውኃ ይዞአቸው ተመለሰ፡፡ በዚህ መሠረት ሾፌሩም ሆነ መኪናው በይርጋዓለም ከተማ አደሩ፡፡ ማታ በተነጋገሩት መሠረት ሾፌሩ ጧት ሌሊት ተነስቶ በረረና ለሥራ እንዲ ደርስ ማቴዎስን ይዞ ተመለሰ፡፡ ቡድኑም ሥራውን በመቀጠል ወደ ሸበዲኖ ወረዳ ሄዶ በፕሮግራሙ መሠረት በለኩ ከተማ ሥራውን ቀጠለ፡፡ ዳሩ ግን ለማቴዎስ ሰበብ እንድትሆን የተፈለገችው ሴት (ወዳጁ) በዚያች ሌሊት ነበር ሞታ ያደረችው፡፡ አንድን ሰው (ማቴዎስን) ለማጥፋት ብለው፣ ከሴትዮዋ ጭምር አምስት ነፍሳት ሞት የተፈረደባቸው በዚያች ሌሊት ነበር። 

   እንግዲህ ማቴዎስ ከቡድኑ ተለይቶ ማደሩን፣ ሰውየው በሚከታተለው ስልት ከአረጋገጠ በኋላ፣ በዚያች ሌሊት ነው ሴትዮዋ እንድትሞት የተፈረደባት፡፡ ብቻዋን አልነበርም የሞተችው፣ ሴትዮዋ ነፍሰ-ጡር ነበረችና በማህፀኗ ውስጥ የነበረው ሕፃን (የማቴዎስ ልጅ) እናትየዋ ስትሞት አብሯት ሞተአል ማለት ነው፡፡ ከዚያም ሌላ በቤት ውስጥ የነበረችው አሮጊት የሴትየዋ እናት በዚያች ሌሊት ነበር የተገደለችው፡፡ የተገደለችበት ምክንያት በውል ባይታወቅም ምስክር እንዳትሆን ፈልገው ሳይሆን አልቀረም የገደሏት የሚል ግምት አለ፡፡ 

ሴትየዋን የገደሏት ሰዎች በቤት ውስጥ የነበረችውን ሠራተኛ ከየት አካባቢ የመጣች መሆኗን ሲጠይቋዋት፣ ከአርሲ አሰላ መሆኑዋን ትነግራቸዋለች፡፡ በዚህ ጊዜ ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዝብ ሰጥተዋት፣ ጧት ሌሊት ተነስተሽ ከዚህ አካባቢ ጥፊ፣ ወደ አገርሽ ሂጂ፣ ካልሄድሽ ግን ትሞቻለሽ ብለው አስጠንቅቋው ከቤት አባረሩአት፡፡ ሌሎቹን ሲገድሉ ይህችን ሰራተኛ ለምን እንዳልገደሉ ምክንያቱ ለእኔ ግልጽ ባይሆንም በተፈጸመው ድርጊት በጣም ደንግጣ ስትሸበር ያደረችው ሴት ጧት ሌሊት ተነስታ ከአካባቢው ትጠፋለች፡፡ በሚቀጥለው ቀን ያንን ቤት ዞር ብሎ ያየው ሰው አልነበርም፣ እንደተዘጋ ውሎ ያድራል፡፡ እንግዲህ ሴትየዋ ከሞተች በሶስተኛው ቀን፣ ማቴዎስ የመስክ ሥራውን ጨርሶ ሲመለስ ጊዜው ገና አልመሸምና (ወደ አሥራ-አንድ ሰዓት አካባቢ ነበር) እንደወትሮ መስሎት ወደ ሴትየዋ ቤት ጐራ ሲል፣ ቤቱ ያለወትሮው በቀን ተዘግቶአል (የንግድ ቤት ስለሆነ በቀን አይዘጋም ነበር)፡፡ ማቴዎስ ገረመውና ቀረብ ብሎ በሩን ቢያንኳኳ የሚከፍትለት የለም፡፡ ሰዎቹን ምን ነካቸው ብሎ በሩን ገፋ ሲያደርግ፣ እንዲሁ መለስ ብሎ የቆየው መዝጊያ ይከፈታል፡፡ ሲገባ በቤት ውስጥ ማንም የለም፡፡ አሁንም ለማረጋገጥ ስለፈለገ ወደ ጓዳ ውስጥ ሲገባ የሴትዮዋና የአሮጊቷ አስከሬኖች በአልጋው ላይ ወድቀው ያገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ደነገጠና ሄዶ ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋል፡፡ እንግዲህ የሴትዮዋ ሞት በይፋ የታወቀው ከዚያ በኋላ ነበር ማለት ነው፡፡ ጐረቤቶቿዋ እስከዚያን ጊዜ አልሰማንም ይላሉ፡፡ እንግዲህ ጥይት ሲተኰስ፣ ሰውን የመሰለ ግዙፍ አካል ሲሞት በመደዳ ተያይዘው ያሉ ቤቶች እንዴት ሳይሰሙ እንደቀሩ ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ለማወቅ የጠየቀም ሰው ወይም ምርመራ ያደረገ ፖሊስ አልነበርም፡፡ 

ስለሆነም ከዚያ በኋላ ሴትዮዋን የገደላት ማቴዎስ ነው የሚል ወሬ ተነዛ፡፡ ወሬውም ቀላል ወሬ አልነበረም፡፡ የሞተችው ሴት ምላሷ ተቆርጦዋል፣ ከንፈሯ ተቆርጦዋል፣ ዓይኖቿዋ ተጐልጕሎ ወጥቷል፣ የፊቷ ቆዳ ተገፍፏል፣ በብልቷ ውስጥ እንጨት (ዱላ) ተተክሎአል…ወዘተ እየተባለ በጣም የሚዘገንን ወሬ ተወራ፡፡ ሐቁ ግን ሴትዋ በጥይት ተመታ ከመሞቷ በስተቀር እነዚህ የተባሉት ድርጊቶች የተፈጸመባት አንድም ነገር አልነበርም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ የተቻለው፣ በጊዜው ከፖሊስ ጋር ደርሰው አስከሬኗን ከአነሱት ሰዎች ነው፡፡ በተለይም በወቅቱ የቀበሌው ሊቀመንበር የነበረው ጌታቸው አይቸውና ጐረቤት የሆነው ተስፋዬ ሐሚጦ መጀመሪያ ደርሰው አስከሬኑን ያነሱት መካከል በመሆናቸው ትክክለኛውን ምስክርነት ሊሰጡ ይችላሉና ጠይቁ፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ፣ ሐቁ ይህ ከሆነ እንዲህ ያለ ውዥንብር ለምን አስፈለገ? የሚል ይሆናል፡፡ መልሱ ማቴዎስ ያን ጊዜ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ሾንጐ አባል በመሆኑ አይታሰርም የሚል ፍራቻ ወይም አባባል ስለነበር ሁኔታውን በማጋነን፣ በድርጊቱ የተበሳጩ ሴቶች ተነሳስተው “ማቴዎስ ይያዝልን፣ ይታሠርልን፣ ይገደልልን”…ወዘተ ብለው ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጥያቄ  እንዲያቀርቡ ሴቶችን ለማነሳሳት ታስቦ የተደረገ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንደነበር ታውቋል፡፡ ከዚያም አልፎ የሴቶች ማህበር መሪዎችን ጠርተው በማነጋገር፣ ሴቶቹ ለሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጡ የተደረገው ጥረት ቀላል አልነበርም፡፡ ሴቶቹ ግን ለሰላማዊ ሰልፍ አልወጡም፡፡ ማቴዎስ ገድሎአል የተባለውንም ፖሮፓጋንዳ ያመኑ አይመስሉም ነበር፡፡ 

ክፍል 2 ይቀጥላል!