Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ማቴዎስ ኮርስሳ ለምን ተገደለ? ክፍል 3 (በቤታና ሆጠሶ)  

ከዚህ በመነሳት ዋና አስተዳዳሪው “አሁን ነፍሴን ልታድን የምትቸለው አንተ ብቻ ነህ” በማለት መንግሥቱ ሸዋዬን መማፀን (መለማመጥ) ጀመረ፡፡ መማፀኑም በቃላት ብቻ ሳይሆን ስልሳ ሺህ ብር ሰጥቶት እንደነበርም ታውቋል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ የአሥር ሺህ ብር የቤት ዕቃና ፎቴ ገዝቶ የሰጠው መሆኑን ተደርሶበታል፡፡ በዚያ ዘመን በአሥር ሺህ ብር የሚገዛው ፎቴ በጣም ከፍተኛ ዕቃ መሆኑን መረሳት የለበትም፡፡ መንግሥቱ ሸዋዬ ይህን ያህል ማለትም በድምሩ ሰባ ሺህ ብር ሲታደል፣ አብሮት የነበረው ገበሬ፣ ወርቁ ሀንቃ ግን ምንም እንደአላገኘ ታውቋል፡፡ ያም ሆኖ የቡድኑ አባላት የነበሩት ሁለቱም ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ድርስ በመሄድ በኮሚቴው ፊት ቀርበው ቃላቸውን ለውጠው ሰጡ፣፡ ስለዚህም ተጠይቆ መንግሥቱ ሸዋዬ ቃሉን ሲሰጥ “ማቴዎስ በዕለቱ (በዚያች ዕለት) ማታ በቤቴ አድራለሁ ብሎ ከእኛ ተለይቶ ሄዶአል፣ የት እንደ አደረ ግን እኛ አናወቅም፡፡ ጧት ሲመጣ ግን በፊቱ ላይ የድንጋጤ መልክ ይታይበታል፣ የመሸበር መንፈስ በፊቱ ላይ ይነበባል፡፡ እንዲያውም ከዚያ በፊት የተደረጉትን ስብሰባዎች በሊቀመንበርነት ሲመራ የነበረው ሰውዬ (ማቴዎስ) በዚያች ዕለት በለኩ ከተማ የተደረገውን ስብሰባ መምራት ስለአቃተው እኔ ነበርኩ ስብሰባውን የመራሁት” ብሎ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ አብሮት የነበረው ገበሬ  ደግሞ “ጓድ መንግሥቱ ሸዋዬ ያለው ሁሉም ትክክል ነው” ብሎ በአጭሩ ዘግቷል፡፡ እዚህ ላይ ያለው ትዝብት መንግሥቱ ሸዋዬ ለሰባ ሺህ ብር ($70 000) እርግጥ ነው በዛሬው ተመን ብዙ መቶ ሺህ ብር ይሆናል፣ እውነትን ሲሸጥ፣ ወርቁ ሀንቃ ግን በዜሮ ሳንቲም ራሱን ሽጦአል፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ለዋና አስተዳዳሪው ሽፋን ሲሰጥ የቆየው እንዳለ ተሰማ (የኮሚቴው ሊቀመንበር) “ታዲያ አሁን ይህ ሰው (ማቴዎስን) ሙሉ በሙሉ አልገደለም ብሎ ለመናገር ይቻላል ወይ?” ብሎ አባላቱን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ኮሚቴው ለመወሰን ችግር ስለገጠመው “ለማንኛውም እስቲ ሾፌሩ ተጠርቶ ይጠየቅ” በሚለው ሐሳብ ላይ ተሰማምተው ሾፌሩን ጠሩት፡፡ ሾፌሩ በበኩሉ ወደ አዲስ አበባ ተጠርቶ በኮሚቴው ፊት ቀርቦ ሲጠየቅ፣ ቀደም ብሎ በአዋሣ ለፖሊስ ሰጥቶት የነበረውን  ቃል አልለወጠም፡፡ ይኸውም “በዚያች ዕለት እኔ ማቴዎስን ያደረስኩት ከአቦስቶ ወደ ማዶ ካለው ወደ ገጠር ቤቱ ነበር እንጂ፣ ወደ አዋሳ አልወሰድኩትም፣ ጧትም ቢሆን ሂጄ ያመጣሁት ከዚያ ከገጠር ቤቱ ነበር እንጂ ከአዋሳ አልነበርም”፣ የሚል ግልጽ የሆነ መልስ ሰጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ክርክር አስነስቶአል፣ ያውም ሾፌሩ ካልወሰደውና ማቴዎስ ወደ አዋሳ ካልሄደ ሴትዮዋን ከየት ደርሶ ሊገድላት ይችላል የሚል ሲሆን፣ ሌሎቹ የፈጠሩት የክርክር ፈሊጥ ግን ማቴዎስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነው፣ የማንንም መኪና አዝዞ ሊወስድ ይችላል፣ ስለዚህ በዚያው መኪና ባይሄድም በሌላ መኪና ሊሄድ ስለሚችል እርሱ አልገደለም ለማለት አይቻልም በማለት ነበር የተከራከሩት፡፡ እዚህ ላይ ነገሩ እንኳን “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ዥግራ” እንደሚባለው ሆኖ ነው እንጂ፣ በአንፃሩ ያለውን ሎጂክ ማየት ነበረባቸው፡፡ በዕለቱ ማቴዎስ የሄደው ገጠር መሆኑ ከታወቀ፣ በገጠር ውስጥ ደግሞ 1ኛ መኪና አለመኖሩን ወይንም የማይገኝ መሆኑ መታወቅ ነበረበት፡፡ 2ኛ ስልክ ደውሎ መኪና አምጡልኝ ብሎ እንዳያዝ በገጠር ስልክ አለመኖሩን መረዳት ነበረባቸው። ታዲያ ይህን ሎጂክ ወደ ክርክሩ ውስጥ ሳያስገቡ እነመንግሥቱ ሸዋዬ በሰጡት ቃል፣ (ያውም ጭብጥ በሌለው በጥርጣሬ) “ማቴዎስ አልገደለም ብሎ ሙሉ በሙሉ ማመን አይቻልም” ወደሚለው ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ያም ሆኖ ያጠራጥራል ነው ያሉት እንጂ ገድሎአል ለማለት አልቻሉም ወይንም አልደፈሩም። ስለዚህ ይህን ችግር ሊፈታ የሚችለው ፍርድ ቤት ብቻ ስለሆነ፣ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት በሚለው ሐሳብ ላይ ሁሉም ተሰማሙ። ለዚህ “ ሲዳማ” ኢሠፓ ነው ተብሎ እነርሱን ምን አጨቃጨቃቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲጣራ በሚለው ተሰማምተው፣ የኮሚቴው ሊቀመንበር  እንዳለው ተሰማ ጉዳዩን ለፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም አቅርቦ ከኢሠፓ አባልነት እንዲሰርዘው በማለት ኃላፊነቱ ለእርሱ ተሰጠ። ምክንያቱ ማቴዎስ፣ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴና የብሔራዊ ሾንጐ አባልም ጭምር ስለነበር፣ ከዚህ ሁሉ ካልተሰረዘ በስተቀር በወንጀል ተከስሶ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ የሌለበት በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከማዕከላዊ ኮሚቴና ከብሔራዊ ሾንጐ አባልነት ሊሰርዘው የሚችል፡ ማለትም ሥልጣን ያለው መንግሥቱ ኃይለማርያም ብቻ ነበር።

በመሆኑም ጉዳዩ ዞሮ ዞሮ ወደ እነእንዳለ ተሰማ እጅ በመግባቱ፣ ማቴዎስን ለማጥፋት ከፍተኛ ጉጉት የነበረው ቡድን በጣም ተደሰተ። ስለሆነም እንዳለው ተሰማ ያንን አጋጣሚ በመጠቀም: አቅርብ የተባለውን ማለትም የኢሠፓ ዲሲፒልን ኮሚቴ በአዲስ አበባ ያጠራውን መዝገብ ደብቆ፣ ቀደም ብሎ ከማዕከላዊ ምርመራ የተላከውን፣ ያውም ፖሊስ ማቴዎስን አሰቃይቶ በአዋሣ ያጠራውንና፣ ማቴዎስ በግድ አምኖ የፈረመበትን መዝገብ ይዞ ነበር ወደ መንግሥቱ ፊት የቀረበው። እንግዲህ ያ መዝገብ ማቴዎስ በድብደባ ተሰቃይቶ ማለትም ቶርቸር በዝቶበት፣ በድን ሆኖ ህሊናውን ስቶ (unconscious) ሆኖ ሳለ እጁን ጐትተው ያስፈረሙትን መዝገብ ነበር። ከዚያ መዝገብ ተዘጋጅቶ የቀረበለትን መግለጫ ከተመለከተ በኋላ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ለማቴዎስ ኮርስሳ የጻፈው ደብደቤ (ሴርቲፍኬት) እንዲህ የሚል ነበር፣ “…ማቴዎስ ኮርስሳ፣ ሰው ገድለህ፣ መግደልህን አምነህ በፈረምከው መሠረት፣ ከዛሬ ጀምሮ ከኢሠፓ አባልነት፣ ከኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴና ከብሔራዊ ሾንጐ አባልነት ተሰርዘሃል” ፊርማ መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚል ነበር። ልብ-በሉ ማቴዎስ በአዲስ አበባ ዲሲፕልን ኮሚቴ ፊት ቀርቦ የፈረመው ምንም መዝገብ አልነበረም። በመሆኑም ማቴዎስን ለማጥፋት ሲዶልት የከረመው ቡድን በዚያን ጊዜ ነበር የመንፈስ እርካታ “እፎይታ” ያገኘው። ስለሆነም ማቴዎስ ወንጀል ወደ ተሠራበት አካባቢ ሄዶ ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተባለና ወዲያውኑ ማለትም በዚያውኑ ዕለት ወደ ማታ ነበር በፖሊስ መኪና ተጭኖ ወደ አዋሣ የተወሰደው።

   በመሆኑም በአዲስ አበባ የማቴዎስን ጉዳይ ሲከታተሉ የነበሩት ሰዎች (ወገኖች) ወዲያውኑ ስልክ ደወሉና “ማቴዎስን የያዘ መኪና አሁን ከዚህ (አ. አ) ተነስቶአል፣ ወደ ማታ አዋሳ ይገባል፣ ምናልባት ጊዜ ሳይሰጡ ነገ ወደ ፍርድ ቤት ሊያቀርቡት ይችላሉና ቶሎ ብላችሁ ጠበቃ ፈልጉ” ብለው አስጠነቀቁ። ማቴዎስ ማታውን ገብቶ ስለአደረ ጧት ዘመዶቹና ጓደኞቹ ወደ አዋሳው ማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ ጣቢያ (እሥር ቤት) ሄደው ሲጠይቁ፣ ማቴዎስን እዛው አገኝተው ስንቅም ሰጥውታል። በዕለቱ ወደ ፍርድ ቤት ይቀርብ ይሆናል የሚል ግምት ስለነበር፣ እዛው እሥር ቤት አካባቢና በከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ሰው ተመድቦ እንቅስቃሴውን ሲጠብቅ ውሎአል። ማቴዎስን ግን ወደ ፍርድ ቤት አላቀረቡትም። በዛው ፅለት ወደ ማታ “ሳትፈርም የተረሳ መዝገብ ስለአለ ወደ አዲስ አበባ ሄደህ ትፈርማለህ” ብለው ይዘውት ወጡ። ዳሩ ግን አዲስ አበባ ቀርቶ ወደ ሻሻመኔም አልደረሰም። በዚያች ሌሊት ነበር ማቴዎስን ከሁለት ተማሪዎች ማለትም ከዘመዱ ልጆች ጋር በቶዮታ መኪና ጭነውት ጥቁር ውኃ ከተሻገሩ በኋላ ከአዲስ አበባ መንገድ ወደ ግራ ታጥፈው፣ ሻመና ወደሚወስደው መንገድ ላይ ወደ ኮርብታው አካባቢ ሲደርሱ፣ ከመኪና አውጥተዋቸው በጫካ ውስጥ ረሽነው በተዘጋጀው ጉርጓድ ውስጥ ጨምረው በቡልዶዜር አፈር አለብሰው ተመልሰዋል። በዚህ ዓይነት ነው ማቴዎስን ያለፍርድ የገደሉት።

እንግዲህ ማቴዎስ ሴትዮዋን ገድሎ ከሆነ ታዲያ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ ምን አስፈራቸው? የዚህ ጥያቄ መልስ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ማቴዎስ የሞተው ሴትዮዋን ገድሎ ሳይሆን “የጐሮሮአችን አጥንት ሆነ” ብለው የደርግ ባለሥልጣናት ማቴዎስን ባልሠራው ወንጀል ሰበብ ፈልገው የገደሉት መሆኑን በአካባቢው የነበረ ሰው ሁሉ በተለይም የሲዳማ ሕዝብ በሙሉ የሚያውቀው ሐቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ማቴዎስን ለመደምሰስ መንገድ ሲያመቻቹ ገዥዎች የአምስት ንጹሐንን ነፍሳት አብሮ መደምሰስ ሞልቶ የተረፈ የጭካኔያቸው መጠን መሆኑን ማየት ይቻላል። ከዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ምን መማር አለበት? ሸፍጥ፣ ተንኮል፤መሰሪነት፤በቀል፤እኔ ብቻ ልኑር ባይነት የአገሪቱዋ ባህል ሆኖ መቀጠል የለበትም። በዛሬው ዓለም በጋራ ተሳስበን ሰርተን መኖር አለብን። በዚች አገር ላይ ዲሞክራሲና የህግ በላይነት ከሌለ የሃገሪቱ ህዝብ በአንድነት ማቆየትን አንችልም። ሰውን መግደል ብቻ ለችግራችን መፍትሄ አይሆንምና።

  

   ኢህአዴግ ገብቶ የፖለቲካ እሥረኞች እስከተፈቱ ድረስ፣ የማቴዎስ ዘመዶች መሞቱን አላመኑም ነበር። ከማቴዎስ ሞት በኋላ ማለትም ሁለት ዓመት አልፎ አንድ ቀን በሐዋሣ ከተማ አቶ ኮርስሳን (የማቴዎስን አባት) አገኘሁትና በብሔራዊ ሆቴል ቡና ጋብዤው ቁጭ ብለን ስንጫወት፣ “ስለ ማቴዎስ ምን ትሰማለህ?” ብሎ ሲጠይቀኝ፣ ምን ዓይነት መልስ እንደምሰጥ ተቸገርኩና ለትንሽ ጊዜ ፀጥ ብዬ ቆየሁ። ምክንያቱም ሞቶአል ብዬ እንዳልነግረው፣ አንደኛ ሰውዬው ማቴዎስ መሞቱን የሚያምን ዓይነት ዝንባሌ አልነበረውም፣ ሁለተኛ በባህላችን መሠረት መርዶ በቤቱ ነው እንጂ ባገኙበት ቦታ አይነገርም። ሆኖም ከትንሽ ጊዜ ጸጥታ በኋላ “ይህን ትተን ሌላ ነገር ብንጫወት ይሸላል” አልኩት። “ምን አልክ?” ብሎ እንደገና ሲጠይቀኝ፣ ደገምኩለት። “አቲ መአፎቶ ህጌ” ማለትም ስለዚህ አንተ ምን ታውቃለህ ወይም ምንም አታውቅም ማለት ነው። እኛ የማቴዎስን ሞት የተረዳነው በማግሥቱ ነው፣ ዘመዶቹ ግን ኢህአዴግ ገብቶ የፖለቲካ እሥረኞች ሲፈቱ ከእነዚያ መካከል ማቴዎስ ዛሬ ወይም ነገ ይመጣል እያሉ ይጠባበቁ ነበሩ፡ ግን አልሆነም፡ ማቴዎስ ከሞተ ጊዜው ቆይቷልና። 

እንግዲህ በዚህ ዘዴ ማቴዎስን ከአስወገዱ በኋላ የሚከራከር በሌለበት (without challenge) የሲዳማን ኢኮኖሚ አውድመው፣ የብሔሩንም ህሉውና ለማጥፋት በከፍተኛ ደረጃ ሲጥሩ እንደነበር ብዙዎቻችን የምናወቃው ጉዳይ ነው። ይህንን በጥሞና ብንመለከት አንደኛ ለሰሜኑ ጦርነት ተብሎ ሚሊሻ በብዛት የሚመለመለው ከሲዳማ ነበር። ይህ ደግሞ የጣምራ ተፅዕኖ አለው፣ 1ኛ ሠርተው ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ጉልበት ያለው ወጣት፣ ለምን እንደሚዋጋ እንኳ በውል ሳያውቅ ወይንም የራሱን ህልውና ለማስከበር ማለትም ከባርነት ነፃ ለመውጣት ሳይሆን፣ የገዥዎቹን ፍላጐቶች ለማሟላት ለሚደረገው ጦርነት ማገዶ  እንዲሆን ሲሆን፣ በሌላኛው መልክ ደግሞ ልጅ ወልዶ የመጪውን ትውልድ የሚተካ ወጣት ወደ ጦር ሜዳ ተወስዶ በመማገዱ የሕዝቡን ቁጥር ለማዳከም ሌላ ምክንያት ሆኖ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የመንደር ምሰረታ (Villagization) በሚል በመሰረተቢስ ፍልስፍና ሕዝቡን ከሞቀ ቤታቸው እያፈናቀሉ በማይሆናቸው ቦታ በማሰባሰብ ኢኮኖሚው እንዲወድምና ሕዝቡም እንዲያልቅ ከፍተኛ ደባ ተሠርቶአል። ይህ ፍልስፍና በሲዳማ ምድር የማይሠራበት በቂ ምክንያት አለው። አንደኛ ሕዝቡ ቋሚ ንብረት አፍርቶ መጀመሪያውኑ በመንደር መልክ የሚኖር ሕዝብ በመሆኑ ንብረቱን ጥሎ ወደ ሌላ መንደር ይሄዳል ማለት በሕዝቡ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል። ሁለተኛው ደግሞ የሲዳማ ሕዝብ ትልቅና ጠንካራ ቤቶች ሠርቶ፣ በስፋት የሚኖር ሕዝብ ሲሆን፣ “መንደር” ተብሎ በአንድ ጠባብ ቦታ ከመሰበሳቡም ሌላ፣ በትናንሽ (ጠባብ) ጎጆዎች ውስጥ በመታጨቁ ሕዝቡ እንዲያልቅ ሌላ ምክንያት ሆኖአል። በመሠረቱ መታወቅ ያለበት የሲዳማ ሰዎች ዕድሜአቸው እየገፋ ሲሄድ “ለሞትና ሕይወት” እያሉ ትላልቅ ቤቶች ሠርተው፣ ተዝናንተው የሚኖሩ መሆናቸው መታወቅ ነበርበት። የዚህ ትርጉም ደግሞ በሕይወት ሲኖሩ ዕድሜአቸው እየገፋ በሄደ ቁጥር ከብዙ ሰዎች ዘንድ እየታወቁ ስለሚሄዱ፣ ያልታሰቡ እንግዶች በድንገት ሊመጡ ስለሚችሉ ወይንም ሌሎች የተቸገሩ ሰዎች ሲመጡ አብዛኛውም ጊዜ ከአዛውንቶች ስለሚጠጉ ቤቱ ጠባብ መሆን የለበትም፣ በሌላ አነጋገር ያንን ሁሉ የሚችል ትልቅ ቤት መሆን አለበት። በሞት ጊዜ ደግሞ አልቃሽ ዘመድና ወዳጅ በብዛት ሊመጡ ስለሚችሉ፣ ያንን ሁሉ የሚያስተናግድ ትልቅ ቤት መኖር አለበት። ከዚህ በመነሳት ነው ሲዳማዎች “ለሞትና ለሕይወት” እያሉ ትላልቅ ቤቶች ሠርተው የሚኖሩበት ምክንያት። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ተነቅለህ በአነስተኛ መንደርና በጠባብ ጎጆ፣ ከልጆችና ከልጆቻቸው ሚስቶች ጋር በአንድ ላይ አፍነው አስቀመጡአቸው፣ ይህ ደግሞ የሲዳማ ባህል የማይቀበለው ወግ ስለሆነ “ይህን ኑሮ ነው ብለን ለመኖር አንችልም” ብለው የምግብ አድማ (hunger strike) በማድረግ የሞቱት አዛውንቶች ብዙ ሲሆኑ፣ የሲዳማ ታሪክ ግን እንደሚያስታውሳቸው አልጠራጠርም። በሌላ በኩል ግን የመንደር ምሥረታ በሲዳማ ውስጥ ያስከተለው  ቀውስ ራሱን የቻለ ትልቅ መጽሐፍ ስለሚወጣው ምርምርና ጥናት (ሪሰርች) እንዲደረግበት እየጋበዝኩኝ ይህን እዚሁ እተዋለሁ።