Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ማቴዎስ ኮርስሳ ለምን ተገደለ?(በቤታና ሆጠሶ) 

ክፍል 2 (ካለፈዉ የቀጠለ)

በወቅቱ ሶስት ሰዎች ነበሩ ፖሊስ ለጥያቄ ብሎ ያሠራቸው፡፡ ዳሩ ግን ማቴዎስ ገድሎአል የሚለው ወሬ በሰፊው ቀጥሎ፣ በጠላ፤ በጠጅና በየቡና ቤቶች የሚወራው ወሬ ይህ ብቻ ሆኖ ቀረ። ማን ማንን እንደሚጋብዝ ወይም ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም፣ ብቻ እየጠጡ ወሬውን ማሞቅ በወቅቱ ለብዙዎቹ ትልቅ ሥራ ሆኖ የከረመው፡፡ ለዚህ ሁሉ ለፖሮፓጋንዳው ዋና ሞተር አንቀሳቃሹ አብርሃም ዘርፉ የተባለ ሰካራም ለአሰተዳደሩ ወሬ በማቀበል የሚተዳደር ሲሆን ሌሎችም ብዙ አጃቢዎች እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ግን ለጥያቄ ተብለው የታሠሩት ሶስት ሰዎች እኛ አልገደልንም ብለው ስለካዱ፣ እንግዲያውስ ሴትዮዋን የገደላትን ሰው በውል ለይታ ለማወቅ የምትችለው በቤቱ ውስጥ የነበረችው ሠራተኛ ስለምትሆን ካለችበት ተፈልጋ ትምጣ ተባለ፡፡ ያችን ሴትዮ ፈልጐ ለማምጣት በፖሊስ ታጅቦ የሄደው፣ በወቅቱ ፖሊሶች ለጥያቄ ብሎ ካሠራቸው ከሶስቱ ሰዎች መካከል አንዱ አብርሃም ገሮ የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የቀድሞው ወታደር፣ አብርሃም ገሮ በወቅቱ በቦርድ ጡረታ የወጣ ሰው ነበር። ከዚያም ያችን ሴት በወዳጅነት ይዞ የቆዬ ሲሆን፣ ኋላ ግን ወደ ማቴዎስ የተቀለበሰችው በሥልጣኑ ስለአስፈራራት ነው በማለት በማቴዎስ ላይ ቅም ይዞበት እንደ ነበርም ተውቋዋል። ይህን ሁኔታ በውል የተረደው ተፈራ እንዳለ፣ ይህን በሰው ግድያ ላይ ተሰማርቶ የቆዬውንና በሰው ሕይወት ላይ ደንታ የሌለውን ግለሰብ ስለአገኘ አብርሃም ገሮን ቅጥረኛ አድርጐ በመጠቀም ነው ተፈራ እንዳለ ሴትዮዋን ያስገደለት የሚል ያልተራጋገጠ ወሬ አለ። ብቻ ያም ሆነ ይህ  አብርሃምና ፖሊሶቹ ሊፈልጉ ሄደው፣ በሶስተኛው ቀን ሴትዮዋን ከአርሲ አሰላ ይዘን አመጣናት አሉ፡፡ እዚህ ላይ የሚገርመው ነገር ቢኖር አድራሻዋ የማትታወቅ ሴት ከሐዋሳ እስከ አሰላ ድረስ ሄደው፣ ያውም በሞጆ ዞረው ነው የሚኬዳው፣ በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ይዘን መጣን አሉ፡፡ እንዴት ቶሎ እንደቀናቸውና አድራሻዋንስ እንዴት እንዳወቁ ማንም አያውቅም፡፡ ይሁንና ይህን በዚህ ትተን ወደ ዋናው ነገር ስንመለስ ሠራተኛዋ ተጠይቃ የሰጠችው ቃል እንደሚከተለው ነበር፣ “ሌሊት ሰው ከተኛ በኋላ የሆኑ ሰዎች መጥተው ከውጭ በሩን አንኳኩ” ትላለች ማስረዳት ስትጀምር፡፡ “ማነው ብዬ ስጠይቅ እኔ ማቴዎስ ነኝና በሩን ክፈች ብሎ ሲናገር፣ ድምጹ ግን የማቴዎስ ድምጽ አለመሆኑን ስለተረዳሁ፣ እኛ ተኝተናል፣ በዚህ ሰዓት በሩ አይከፈትም ብዬ ስነግረው፣ ምን ነካሽ አሁን ተነስተሽ ክፈች እንጂ ብሎ በቁጣ ቃል ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ ሴትዮዋ ምን እንደምትል ለመስማት ፈለኩና ወደ ጓዳ ገብቼ እመቤቲቱን ሳማክራት፣ ማቴዎስ ነኝ ካለ ምን ቸገረሽ ሂጂና ክፈች ስትለኝ፣ ሂጄ በሩን ከፈትኩና አንገቴን ወጣ አድርጌ ሳይ ሶስት ሰዎች ከግርግዳው ተጠግተው ቆመዋል፣ ጊዜው ጨረቃ ስለሆነ በግልጽ ይታዩ ነበር፣ አንደኛው የደንብ ልብስ (የኢሠፓ ካኪ ማለት ነው) ለብሶአል፣ በራሱ ላይ ባርኔጣ አድርጓል፣ ሌሎቹ ሁለቱ ተራ ልብስ ነው የለበሱት፣ በራሳቸው ላይ የሞተር ብስክሌተኞች ቆብ (helmet) አድርገዋል፡፡ ወዲያውኑ በቅጽበት ቶሎ ብለው ወደ ቤት ገቡ፡፡ ቀጥታ ወደ ጓዳ ገብተው ሴትዮዋን ገደሏት፣፡ በዚህ ጊዜ አሮጊቷ ደንግጣ ወይኔ ልጄ ብላ ዘላ ወደ ጓዳ ስትገባ እርሷንም እዚያው ገደሏት፡፡ ከዚያም ወደ እኔ ተመለሱና ከየት አካባቢ እንደመጣሁ ጠይቀውኝ፣ ለትራንስፖርትና ለስንቅ የሚሆን ገንዘብ ሰጥተውኝ ጧት ሌሊት ተነስተሽ ከዚህ አካባቢ ጥፊ፣ ወደ አገርሽ ሂጂ አለበለዚያ ትሞችያለሽ ብለው አስጠንቅቀውኝ ሄደዋል”፡ ብላ ቃሉዋን ሰጥታለች፡፡ “እንግዲያውስ ሴትዮዋን የገደላት ማቴዎስ ነው ማለትሽ ነዋ?” ብለው ሊያሰምኑዋት ሲሞክሩ፣ ‘ማቴዎስ አይደለም” ብለ መልስ ሰጥታለች፡፡ “እኔ ማቴዎስ ነኝና በሩን ክፈችልኝ ብሎዋል ብለሽ የለም ወይ?” ብለው ሲጠይቋት፣ “ነኝ አለ እንጂ ግን ማቴዎስ አይደለም” ስትላቸው፣ “ጊዜው ሌሊት ነበር እርሱ ግን ማቴዎስ ነኝ ብሎዋል ብለሻል፣ አለመሆኑን እንዴት ታውቂያለሽ” ብለው ሲጠይቋት ሴትዮዋ የሰጠችው መልስ “ጊዜው ሌሊት ይሁን እንጂ ደማቅ ጨረቃ ስለነበር ሁሉም ነገር በግልጽ ይታይ ነበር። እኔ ማቴዎስን በመልክ ቀርቶ በድምፅም ልለይ እችላለሁ፡ ከዚህም በላይ ያ ሰውዬ በጣም አጭር ነው፣ ቁመቱ የማቴዎስን ቁመት አይደርስም፣ ስለዚህ ማቴዎስ አይደለም” በማለት ስትከራከር፣ ነገሩ እነሱ በፈለጉት መንገድ ሳይሄድላቸው ስለቀረ ሴትዮዋን ወደ መጣሽበት አገር ሂጂ ብለው አሰናበቷት። ከዚያ በኋላ ያች ሴት የት እንደደረሰች፤ በሕይወት ትኑር ወይም አትኑር የሚታወቅ ነገር የለም።

በሌላ በኩል ደግሞ በጥርጣሬ የተያዙት ሰዎች ወዲያውኑ ተለቀቁ፡፡ ስለዚህ ትኩረቱ አሁንም ቢሆን በማቴዎስ ላይ ብቻ ሆነ፡፡ ስለሆነም በዚያች ማታ ማቴዎስን ወደ አዋሣ አድርሰሃል፣ በመሆኑም ሴትዮዋን የገደላት ማቴዎስ ነው ተብሎአልና ምን ታውቃለህ ተብሎ ሾፌሩ ተጠየቀ፡፡ ለዚህ ጥያቄ ሾፌሩ የሰጠው መልስ “በዚያን ዕለት እኔ ማቴዎስን ወደ አዋሣ አልወሰድኩትም፣ እኔ እርሱን ያደረስኩት አቦስቶ አጠገብ ወደአለው ወደ ገጠር ቤቱ ነበር፣ ጧትም ቢሆን ሂጄ ያመጣሁት ከዚያ ከገጠር ቤቱ ነበር” የሚል ነበር መልሱ፡፡ በዚህ ሁኔታ ሾፌሩ በተደጋጋሚ ተጠይቆ፣ ቃሉን አልለወጠም፡፡ በዚያን ዕለት ማታ ሾፌሩ ማቴዎስን ወደ አዋሣ የወሰደ ይመስላችኃል ወይ ተብለው የተጠየቁት የቡድኑ አባላት ማለትም እነመንግሥቱ ሸዋዬ የሰጡት መልስ፣ “ሾፌሩ ማቴዎስን ወደ ቤቱ አድርሶ የተመለሰው አርባ ደቂቃ ባልሞላበት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አዋሣ ደርሶ ተመልሶአል ብለን እኛ አናምንም” በማለት ጠንካራ መልስ ሰጥተው ነበር፡፡ “ከዚያስ ሌሊቱን ተመልሶ ወስዶት እንደሆነ ምን ታውቃላችሁ?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “እርግጥ ሾፌሩ ከእኛ ጋር አላደረም፣ በቤቱ ነበር ያደረው፣ መኪናው ግን እኛ በአደርንበት ሆቴል ግቢ ውስጥ ነበር ያደረው፣ ሌሊቱን በሙሉ ከግቢው አልወጣም” የሚል  መልስ ስለሰጡ፣ ነገሩ (ጉዳዩ) አሁንም መርማሪዎቹ በፈለጉት መንገድ ሳይሄድላቸው ቀርቶዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን “ ማቴዎስ በሴትዮዋ ላይ የፈጸመው ድርጊት በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ድርጊት ነው” እያሉ የፈጠራ ወሬአቸውን ቀጠሉበት፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን አስቀያሚ ድርጊቶች እየዘረዘሩ፣ “በሰው ልጅ ላይ የማይደረጉ ጨካኝ የአረማኔ ተግባራት ናቸው፣ ስለዚህ ማቴዎስ መያዝ፣ መታሠርና መገደል አለበት” የሚለው ቅስቀሳ በሰፊው ታካሄደበት፡፡ ለዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ምንም እንኳ አብርሃም ዘርፉ ዋና ሞተር ቢሆንም፣ ቃሉን የሚያስተጋቡ ሌሎችም ከ12 በላይ የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ነበሩት። በተለይም በቦዘኔውና በተራ ሰው (Laymen) አካባቢ ስብከቱ በጣም የጋለ ነበር፡፡ ምን ቸገራቸው እነርሱ ጊዜያዊ ሥራ አግኝተዋልና፡፡ ምንም እንኳ ተጠቃሚዎቹ ጥቂቶች ቢሆኑም፣ ለፖርፓጋንዳው የተረጨው ገንዘብ በእውነቱ ጥቂት አልነበርም፡፡ ዓላማው ሴቶችን ለሰላማዊ ሰልፍ ለማስነሳሳት ቢሆንም ሴቶቹ ግን ግብታዊ ወይም (emotional) አልሆኑም፣ ይልቁንም ምክንያታዊ (rational) ሆኑ እንጂ፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ የተደረገው ቅስቀሳና ፖሮፓጋንዳ የተጠበቀውን ውጤት ሳያስገኝ ቀርቶአል፡፡

   በመጨረሻ ላይ ባወጡት ዕቅድ መሠረት “ማቴዎስ ሊጠፋ ነው፣ ዛሬ ወይም ነገ ካልታያዘ በስተቀር መጥፋቱ የማይቀር ነው” በማለት በዘዴ የተቀነባበረ ወይም በሐሰት የተቀናጀ ስልክ፣ ከኢሠፓ ጽ/ቤት፣ ከአገር አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ከፖሊስ ዋና መምሪያና ከሕዝብ ደህንነት ጽ/ቤት ወደ አዲስ አበባ በመደወልና ሽብር የተፈጠረ በማስመሰል ሁኔታው እንዲለወጥ ለማድረግ ችሎአል፡፡ ስለሆነም “እንግዲያውስ በቁጥጥር ሥር አድርጉትና ምርመራው ይቀጥል” የሚል መልስ ሲሰጣቸው፣ “የኢሠፓ አባል በወንጀል ተከስሶ አይታሠርም” የሚለው ሐረግ በማቴዎስ ላይ ሲጣስ ማንንም አላስገረመውም፣ ምክያቱም “አባላት ሁሉ እኩል ናቸው፣ አንዳንዶቹ ግን  ይበልጥ እኩል” ናቸውና ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ድል ከመጠን በላይ የተደሰቱ የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ባለሥልጣናት ይህንን መልስ ባገኙ ማግሥት ስብሰባ አለ በማለት ኢሠፓ ጽ/ቤት እንድትመጣ ብለው ማቴዎስን በስልክ ይጠሩታል፡፡ ደጉ ማቴዎስ እውነትም ስብሰባ ያለ መስሎት ሲሄድ፣ ከደቡብ ዕዝ ተዘጋጅቶ በኢሠፓ ጽ/ቤት ከግርግዳው ሥር ተጠግቶ ይጠባበቅ የነበረው ልዩ ኮማንዶ (ከፖሊስ አልፎ ልዩ ኮማንዶ ለምን እንዳስፈለገ የሚያውቅ የለም) በድንገት ዘለው በማቴዎስ አንገት ላይ ጉብ ይሉበታል፡፡ ከዚያም አንጠልጥለው ይዘውት ይሄዱና የሐዋሣ ማዕከላዊ በሚባለው ቦታ ያስሩታል፡፡ ከዚያም በመቀጠል በማቴዎስ ቤት ሆነው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩትን ሁለት የዘመዱ ልጆች ተባብራችሁ ገድላችኋል በማለት ከቤቱ ታፍነው ከእርሱ ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡

   ከዚያም ምርመራው ይቀጥልና ማቴዎስን ከመጠን በላይ ያሰቃዩታል፡፡ “ገድያለሁ ብለህ እመን” እያሉ ይገርፉታል፣ በኤሌክትሪክ ያቃጥሉታል፣ እግሮቹን ይተለትላሉ፡፡ ስቃይ (torture) ሲበዛበት ማቴዎስ ገድያለሁ ብሎ ያምናል፡፡ እንግዲህ ማቴዎስ አምኖ ስለፈረመ በለሥልጣኖቹ  ከመጠን በላይ ተደሰቱ። ደስታቸውን በውስጣቸው እንኳ አምቀው ለመያዝ ስለአልቻሉ በይፋ ሲናገሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ የክፍለ ሀገሩ ዋና አስተዳደሪ በዚያን ሰሞን ነበር ወደ ምክትል አስተዳደሪው ማለትም ሻለቃ መብዓጽዮን (ጃተኒ አሊ) ቢሮ ድረስ ሄዶ “ማቴዎስ ሴትዮዋ መግደሉን አሁን አመንክ ወይ?” ብሎ የጠየቀው፡፡ መብዓጽዮን ግን አሁንም ቢሆን አላምንም የሚል መልስ ነበር የሰጠው። ይህን ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳው ምክንያት፣ በወቅቱ ማቴዎስ ሴትዮዋን አልገደለም ብለው ከሚከራከሩት ጥቂት ከክፍለ ሀገሩ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ሸለቃ መብዓጽዮን በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ባለቤቱ ያመነውን አንተ አላምንም ለማለት እንዴት ትደፍራለህ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ ሻለቃው የሰጠው መልስ “አዎን እኔ አላምንም ብዬአለሁ፣ የማላምንበትም ምክንያት ስለአለኝ ነው” የሚል ነበር መልሱ፡፡ “ታዲያ አንተ መቼ ነው የምታምነው?” ብሎ ሲጠይቀው፣ “እኔ የማምነው ሰውዬው (ማቴዎስ) ወደ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተመስክሮበት፣ ብያኔ ሲሰጥበት ብቻ ነው” ብሎ ሻለቃው ሲመልስለት፣ ዋና አስተዳዳሪው በጣም ተናዶ ወደ ራሱ ቢሮ ተመልሶዋል፡፡ አስታውሱ ከዚያ በፊት ጉዳይ ሲኖረው፣ ወደ ራሱ ቢሮ ጠርቶ ወይንም በስልክ ያነጋግራል እንጂ፣ ዋና አስተዳዳሪው ወደ ምክትሉ ቢሮ በፊጹም አይሄድም ነበር። ምክንያቱሳ ቢባል፣ ሁለቱም ሰለማይግባቡና በመካከላቸው በጣም የከረረ የሐሳብ ልዩነት ስለነበር ነው፡፡ ያን ዕለት ግን “ማቴዎስ ወንጀሉን አመነ” ስለተባለ የደስታው ብዛት ራሱን አዙሮት፣ ወዴት እንደሚሄድ በውል ሰያወቅ ነበር ወደ ምክትሉ ቢሮ የገባው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢያን እንዲረዱልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር፣  በማሰቃየት (በቶርቸር) አሳምነውት “ማቴዎስ ወንጀሉን አምኖዋል” በማለት ጠላቶቹ (በዝበዦቹ) ምን ያህል እንደተደሰቱና ፍትህ ናፈቂዎች ግን ምን ያህል እንደአዘኑ ለማወቅ ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ በጣም የሚያሳዝነው ግን ማቴዎስ ወደ ፍርድ ሳይቀርብ፣ እውነቱ ሳይገለጽ፣ ብያኔ ሳያገኝ መሞቱ ነው፡፡

   እርግጥም  በአብዮቱ አፍላው ጊዜ በፖለቲካ ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያለ ፍርድ የሞቱ መሆናቸው የሚካድ ባይሆንም፣ የማቴዎስን ግን ልዩ የሚያድርገው ተሰራ የተባለው ወንጀል ነፍስ ግድያ እንጂ ፖለቲካ አይደለም። ስለሆነም ግድያው የኮሚንስቶች ፖለቲካ ልዩነት ሳይሆን ለብዝበዛ እንዲመቻቸው ስለፈለጉ ብቻ ከጉያቸው አወጥተው የገደሉት መሆኑ ነው፡፡ የማቴዎስ አሟሟት በብዙዎች ዘንድ እንደ እንቆቅልሽ ሆኖ ቀርቶአል፡፡ ይሁንና ማቴዎስን በዚህ መልክ በሥቃይ ከአሳመኑት በኋላ ለፍርድ ሳይቀርብ፣ ውሳኔ ሳይሰጥ ዝም ተብሎ ለረዥም ጊዜ በእሥር ቤት አስቀመጡት፡፡ ምክንያቱም ሥቃይ በዝቶበት ራሱ ከአመነው በስተቀር፣ ማቴዎስ ገድሎአል የሚል አንድም ምስክር አልተገኘምና ነው፡፡ ጉዳዩ ይህ ሆኖ ሳለ ማቴዎስ ወደ ፍርድ ቤት ቢቀርብ፣ በፍርድ ነፃ እንደሚለቀቅ ለማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህ ፍራቻ ማቴዎስን ለፍርድ ሳያቀርቡ፣ እዚያው እሥር ቤት ለረዥም ጊዜ ያስቀምጡታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ መፍትሔ ሊሆን አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል ግን ማቴዎስ ወንጀሉን አምኖ ፈርሞአል ከተባለ በኋላ ጥበቃው (ቁጥጥሩ) አየላለ መሄድ ጀመረ፡፡ ይህም ሲባል በአፍላው ጊዜ ለማቴዎስ የሚሄድለት ስንቅ በጥብቅ ይፈተሽ የነበረው ሁኔታ መላላቱን ለመጠቆም ያህል ነው። በእሥራቱ የመጀመሪያ አካባቢ በወተት ጮጮ ውስጥ ሳይቀር፣ ማማሰያ መሳይ እንጨት (ዱላ) እየከተቱ በወተት ውስጥ ምን ተደብቆ እንደሆነ ይፈትሹ የነበሩት ላልቶአል ማለታችን ነው፣፡ እንዲሁም ስንቁን የሚወስድለት ሰው በሃምሳ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ፣ ስንቁን ለዘበኛ ሰጥቶ ይመለሳል እንጂ ወደ አጥር ግቢ ቀርቦ የማቴዎስን ፊት አያይም ነበር፡፡ ኋላ ግን ጊዜው እየቆየ ሲሄድ ይህ ሁኔታ ተለወጠና ማቴዎስም የሚሄድለትን ሲጃራና ሌሎችን ነገሮች ለዘበኞች እየሰጣቸው (እያጋራ) ቀስ በቀስ መግባባት ጀመረ፡፡ ስንቅ የሚወስድለት ሰው እስከ አጥሩ በር ድረስ በመሄድ  ከማቴዎስ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በመነጋገር ስንቁንም በቀጥታ በእጁ መስጠት ተጀመረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በወተት ጮጮ ውስጥም እንጨት እየከተቱ ማማሰሉም ቀረ፡፡ ይህን አጋጣም በመጠቀም ማቴዎስ አንድ ቀን ከሰውነቱ በኤሌክትሪክ ተቃጥሎ (ተጠብሶ) ከእግሩ ጫማ (Sole) ተተልትሎ የወጣውን ሥጋ (ቆዳ)  ወተት በሄደለት ጮጮ ውስጥ አድርጐ ልኮ ነበር፡፡ የሥጋው ብዛት በሕይወት ካለ ሰው ተተልትሎ የወጣ ሥጋ ነው ብሎ ለማመን በጣም ያስቸግራል፡፡ ብቻ ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሳህን ሞልቶ የሚተርፍ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ ይህ የተተለተለው ሥጋ (ቆዳ) በሕይወት ካለ ሰው ተተልትሎ የወጣ ሥጋ ነው ብሎ ማንም ሊያምነው አይችልም፡፡ ያንን የተመለከተ ሁሉ፣ ሰቆቃ የማይሰማው ወይም የማይሰቀጥጠው ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ ይህን ለማለት የበቃሁበት ምክንያት፣ እኔ አሁንም ወደ ኋላ ተመልሼ በዓይነ-ህሊናዬ ያንን በማስታውስበት ጊዜ በእውነቱ ሰውነቴን ይሰቀጥጠኛልና ነው፡፡

   ይህ ዘገባ ምናልባት የተጋነነ (exaggerated) ይመስል ይሆናል፡ ሐቁ ግን እንዳለ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ይበልጥ ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ በወቅቱ ይህን ካዩት አንዱ ጌታሁን ሲዳ ጥሩ ምስክር ሊሆን ስለሚችል ማነጋገር ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ያንን ቆዳ ለሻለቃ መብዓጽዮን አሳይተነው በቁጭት ተመልክቶአል። ከዚያ በኋለ ነው ዋና አስተዳዳሪው እስከ ምክትሉ ቢሮ ድረስ ሄዶ ሊያሳምነው መሞከሩን የነገረን። በሌላ በኩል ግን ከዚህ ለመማር የምንችለው ነገር ቢኖር፣ የሰው ልጆች ከአውሬዎች ሁሉ የባሱ ጨካኝ አውሬዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ምክንያቱም አውሬዎች ከራሳቸው ወገን ያልሆነ አውሬ ለይተው ነው የሚበሉት እንጂ ከራሳቸው ወገን የሆነውን እንደማይበሉ ግልጽ ነው። ለምሳሌ አንበሳ ሌሎች አውሬዎችን እያደነ ይበላል እንጂ አንበሳን መልሶ አይበላም፣  ሰው ግን የሰውን ሥጋ እንደሚበላ ከእነዚህ እንረዳለን፡፡ እንግዲህ ይህን እዚሁ ትተን ወደ ዋናው ነገር ስንመለስ፣ ማቴዎስ ከሰውነቱ ተቀርፎ የወጣውን ቆዳ ሲልክ፣ በሲጃራ ፓኮ ወረቀት ላይ አጭር ማስታወሻ ጽፎ ነበር፡፡ የሲጃራው ወረቀት ተገልብጦ የተጻፈው ማስታዎሻ እንዲህ ይላል፣ “ወገኖቼ ይህን ከእግሬ ተጠብሶ (ተተልትሎ) የወጣውን ሥጋ ተመልከቱ፣ ሥቃይ (ቶርቸር) ስለበዛብኝ መቋቋም አቅቶኝ፣ በድብደባ ተሰቃይቼ ከምሞት በጥይት ይግደሉኝ በማለት የሰጠሁት ቃል ነው እንጂ፣ ወንጀሉ እኔ የፈጸምኩት አለመሆኑን ተረድታችሁ፣ አቤቱታ ለማሰማት የሚቻልበት ሁኔታ ከአለ፣ አምኖአል ብላችሁ እንዳታቋርጡ አደራ እላለሁ” የሚል ነበር፡፡

   ከላይ እንደጠቀስኩት ማቴዎስ ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለረጅም ጊዜ ታሥሮ ቆይቶአል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ባለሥልጣናቱን ማነጋገር ጀምሮ ነበር፣ አንዳንዶቹ ነስፍ ገዳይ ከሆነ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ሲሉ፣ ሌሎች ግን የውስጥ ችግር የተረዱት ማለትም ምስክር አለመኖሩን የተገነዘቡና በሌላ በኩል ደግሞ የማቴዎስን ነፃነት የማይፈልጉ ወገኖች ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እንደ ፖለቲካ እሥረኛ ሆኖ፣ በእሥር ቤት ያለገደብ እንዲቀመጥ ፈለጉ፡፡ በመሆኑም ነገሩ በመጠኑም ቢሆን ሁለቱን ቡድኖች አነታርኳቸው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት  ማቴዎስ ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ በኢሠፓ ዲሲፕሊን ኮሚቴ አማካይነት ጉዳዩ እንደገና እንዲጣራ ተባለ፡፡ በዚህ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ወስደውት ሲያጣሩ፣ ማቴዎስ ከወንጀሉ ነፃ የሚሆንበት አዝማሚያ ታይቶ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ወንጀሉ ወደ ተፈራ ይዞራል የሚል ፍራቻም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአጣሪውን ኮሚቴ በሊቀመንበርነት ሲመራ የነበረው የጉቦ ሽርኩ የኢሠፓ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ዋና ኃላፊ እንዳለ ተሰማ፣ ለሲዳሞ ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ ሽፋን ሰጪ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ እንዳለ ተሰማ በጣም ዘረኛ ከመሆኑም ሌላ አላዋቂነቱን የማያውቅ ግብዝ ሰው ነበር። ይህ ሰው አገር አስተዳዳሪ የነበሩትን ሁለት ኦሮሞች ማንም ሳያውቅ ዝዋይ ጫካ ውስጥ አስገድሎ አሸዋ ያለበሰ ሰው ነበር። ለምን? ቢባል እሱ ብቻ ነው የሚያውቀው። በመሆኑም የማቴዎስ ጉዳይ ሌላ አቅጣጫ እየያዘ ያለ መሆኑን ለዋና አስተዳዲሪው አስረድቶ ቶሎ ብሎ መፍትሔ እንዲፈልግ አስጠንቅቆት ነበር፡፡ በዚህ ክፉኛ የተደነገጠው አቶ ተፈራ ተሯሩጦ፣ አንድ ዘዴ አገኘ። ይኸውም ያኔ ከማቴዎስ ጋር ወደ መስክ ወጥተው የነበሩት የቡድኑ አባላት ቀርበው ትንሽ ድጋፍ ከሰጡ ሽፋን ሰጪው (እንዳለ ተሰማ) ነገሩን መስመር ለማስያዝ እንደሚችል ቃል ስለገባለት ትኩረቱን በዚህ ላይ አደረገ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ሁለቱም ማለትም ተፈራ እንዳለና እንዳለ ተሰማ ተሰማምተው፣ የቡድኑን አባላት ለማስማማት አቶ ተፈራ ጥረት እንዲያደርግ ሁለቱም ተዋዋሉ፡፡

ክፍል 3 ይቀጥላል!