Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በወቅታዊ የአገራችን እና የሲዳማ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የሰጠው የአቋም መግለጫ!

የሲዳማ ብሔር ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር ለበርካታ ዓመታት ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በትግሉም በርካታ የብሄሩ ተወላጆች በተለያዩ ጊዜያት የእስራት፣ስደት እና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፣እየከፈሉም ይገኛሉ። በ1994 ዓ. ም በሐዋሳ ከተማ ሎቄ በሚባል አካባቢ 'ክልል ይገባናል ብለው ቅጠልና ሳር በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ንጹሃን የሲዳማ ተወላጆች ላይ የመንግስት ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ከመቶ የሚበልጡ ወገኖቻችን በአንድ ቀን በጥቂት ሰአታት ውስጥ ያለቁበት ክስተት የሲዳማ ብሎም አጠቃላይ የአገራችን ህዝብ የማይረሳው ነው። ለበቀል መነሳሳትን የማያውቀው ይህ ታጋሽ ህዝብ "ሆላ ሀላሌሆ" ብሎ አይኑን ወደ ፈጣሪ በማንሳት አስከረኑን በመቅበር ከልቡ የማይጠፋውን ጠባሳ ይዞ ሰላማዊ የትግል ጉዞውን ቀጥሎአል።

ይህም ሆኖ ግን የሕዝቡን ህገመንግሥታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ የሚያስተናግድ የመንግሥት አካል ባለመኖሩ ጥያቄው እስከ አሁን ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ከዚሀ ቀደም በህጋዊ መስመር የቀረበው ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ ምክንያትም ህዝቡ ተጨማሪ መስዋዕትነት እየከፈለ አስፈላጊውን ትግል እያካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክኒያት የሲዳማ ሕዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ሐምሌ 11 2010 ዓ. ም በዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ጸድቆ ወደ ክልል ምክር ቤት ዳግም ተልኳል። የክልሉም ምክር ቤት ከጥቅምት 20 እስክ ጥቅምት 24 2011 ዓ. ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 4ኛ የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ የሲዳማ ብሔር ክልል የመሆን ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ እንዲፈፀም ውሳኔ አሳልፏል። ይኸውም ውሳኔ በመንግስት ተፈፃሚ ሳይሆን በመቆየቱ ሕዝቡ እና የሲዳማ አዲሱ ትውልድ ኤጄቶ በሠላማዊ መንገድ በሰለጠነ አኳሃን ለመንግሥት ቅረታውን እያሰማ ይገኛል።

ይህን ተከትሎ ህገመንግሥታዊ የመብት ጥያቄን በሠላማዊ መንገድ የጠየቀው ሕዝብ በተለያዩ አካላት የመንግስትን ጨምሮ ከፍተኛ የጥላቻ፣ የማንቋሸሽ፣ የማሸማቀቅ፣ ስም የማጥፋት እንዲሁም የመብት ጥሰት እየተፈጸመበት ይገኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት የህዝቡን ጥያቄ በህገመንግሥቱ መሠረት በመመለስና የሚጠበቅበትን በመወጣት እንዲሁም ህዝቡን ከሌሎች የጥፋት ሀይሎች ዘመቻ ለመከላከል አልቻለም ወይም አልፈለገም። #በዓለም ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈጸመባቸው ህዝቦች በመጀመርያ ይደርስባቸው የነበረው የተቀናጀ የጥላቻ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በመሆኑ ይሄው ህዘባችን ላይ ትኩረት ያደረገው ድርጊት መቆም እንዳለበት ለማሳሰብና የኢትዮጵያ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በአስቸኳይ መመለስ እንዳለበት ለማሳሰብ በመላው ዓለም የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጅ ኢትዮጵያዉን ዳያፖራ ማህበራት በግንቦት 5/2019 ዓ. ም (እ.አ.አ) አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በወቅታዊ የኢትዮጵያ በተለይም የሲዳማ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የሚከተለውን ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

1ኛ. የሲዳማ ብሄር ክልል የመሆን ህገመንግሥታዊ ጥያቄና በዞኑ እና የዞኑ የአስተዳደር ክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከተሞች መካከል ያለውን ትስስር በውል ያልተገነዘቡ አካላት የዞኑ ማዕከል በሆነችው በሀዋሳ ከተማ ውስጥ ሰላም እንደጠፋ አስመስለው በተለያዩ ቅጥረኞችና ነውጠኞች የሚያደርጉትን የፕሮፖጋንዳ ሴራ አጥብቀን እንቃወማለን። እነዚሁ አካላት በከተማው ውስጥ የሚፈልጉት አይነት ረብሻ እንዲፈጠር የማይፈነቅሉት ድንጋይ ስለማይኖር ሰላም ወዳዱ የሀዋሳ ህዝብ በንቃት የከተማውን ሰላም እንዲጠብቅ እንጠይቃልን፡፡

2ኛ. የሲዳማ ህዝብ ሕጋዊ የመብት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በመጠየቁ ብቻ የተቀናጀ የሚመስል ዘመቻ በመክፈት ስም የማጥፋትና የማጥላላት ሥራ ላይ የተሰማሩትን ጸረ-ፌዴራል ኃይሎች አጥብቀን እንቃወማለን፤ እንዲሁም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እናባስባለን ።

3ኛ. ከሕግ ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀ የሚገኘውን የሲዳማ ሕዝብ እና የኤጄቶን ጥያቄ እንደግፋለን፤ አፋጣኝ ምላሽ እንድሰጥም እናሳስባለን።

4ኛ. ለበርካታ ዘመናት ተጋብቶና ተዋልዶ በመልካም ጉርብትና በአንድነት የሚኖሩ የዎላይታና የሲዳማ ሕዝቦችን ለማለያየት የዎላይታን ህዝብ እንደከለላ በመጠቀም በስሙ የሚነግዱ ኃይሎችን አጥብቀን እየተቃወምን ስራና ሠላም ወዳዱ የወላይታ ህዝብና በመላው ዓለም የሚኖሩ የወላይታ ምሁራኖች በስሙ የሚነግዱ አካላትን እንዲያወግዙ በአጽዕኖት እንጠይቃለን። እንዲሁም በሲዳማ ሕዝብና በኤጄቶ ስም በወንድም የዏላይታ ሕዝብ ላይ ማናቸውንም ዓይነት አሉታዊ ቅስቀሳወችን የሚያደርጉ ግለሰቦችን አጥብቀን እየተቃወምን እነዚህ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንድታቀቡ ጥሪ እናስተላልፋለን።በመንግስት አካላትም በኩል በህዝቦች መካከል ቅራኔ እና ጥላቻ እንዳለ በማስመሰል የግል የፓለቲካ ጥቅማቸውን ለማግኜት የሚሯሯጡ አካላት ከማይሳካ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እናሳስባለን፡፡

5ኛ. የደ/ብ/ብ/ህ/ክ መንግሥት ም/ቤት ያሳለፈውን ዉሳኔ በማክበር እና የአገራችን ህዝቦች የጋራ የቃልኪዳን ሰነድ ህገመንግስት መሠረት የፌዴራል መንግስትና ምርጫ ቦርድ በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ የህዝብ ውሳኔ (Referendum) በማካሄድ የህዝቡን ጥያቄ በአፍጣኝ ምላሽ እንድሰጥ አጥብቀን እንጠይቃለን።

6ኛ. የሲዳማ ህዝብ በህገመንግስቱ መሰረት የራሱን ክልል ለመመስረት የሚያደርገውን ጉዞ እንዲያግዝ እና የተለያዩ ተያያዥ ስራዎችን እንዲሰራ የተቋቋመው ሴክረተሪያት ጽ/ቤት እስካሁን የተሰሩ ሥራዎችንና ለሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተዘጋጀዉን የህገመንግሥት ሰነድ በፍጥነት ለህዝብ ውይይት እንዲያቀርብ እናሳስባለን፡፡ መንግስት ህገመንግስትን በመጣስ በቀረው ጥቂት ወራት ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ባያደራጅ ህዝቡ መከተል ያለበትን ሁሉንም አይነት ህጋዊ አማራጮችን ከወዲሁ ለህዝቡ እንዲያቀርብ እና ህዝቡ የጋራ ጉዳዩ ላይ በጋራ እንዲወስን እንዲደርግ እንጠይቃለን፡፡

7ኛ. አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች አገር መሆኗን ከግምት ያስገባ የመንግሥት አወቃቀርና ስርዓት ከመተግበር ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደማይኖር በመገንዘብ ለሕዝቦች እኩልነት አመቺ የሆነውን የፌዴራል ስርዓት በተሟላ መልኩ የቡድኖች እና የዜጎችን ክብር እንዲሁም መብት በሚያረጋግጥ መንገድ ተግራባዊ እንዲደረግ እንጠይቃለን። ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ በመንግስትም ሆነ በሌላ ማንኛውም አካል የሚደረግ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴና ዘመቻ አዋጪ እንደማይሆን በመገንዘብ የሕዝባችን ሠላም እና እድገት የተጠበቀ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ እንጠይቃለን። ከህዝቦች እኩልነት አላማ ውጭ ከሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ጋር ህዝባችን የሚያድርገውን ትግል መደገፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

8ኛ. አገራዊ ደህንነትና ሠላም ለሕዝቦች ብልጽግና እንዲሁም ለዲሞክራሲ ማበብ ወሳኝ በመሆኑ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና ሥርዓት አልበኝነት ችግሮችን ከሕዝቡ ጋር በመመካከር እንዲፈታ እንጠይቃለን። በተጨማሪም በሕዝቦች የሚጠየቁ ማናቸውም ህጋዊና ሠላማዊ የመብት ጥያቄዎች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በፍጥነት ምላሽ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።

የሲዳማ ዳያስፖራ ማህበረሰብ
ግምቦት 12, 2019 ዓ. ም
ከመላው ዓለም!