Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ተጠናክሮ የቀጠለውና የከፋው ወረራ በሲዳማ

June 4, 2018

“… የምኒሊክ ወራሪ ኃይል በሲዳማና በኦሮሚያ ጦርነት ባወጀ ጊዜ ቀለብ የሚሰፍርላቸው ስላልነበር የተወረው የአካባቢው ህዝብ ቀለብ አቅራቢ ሆነ፡፡ … ወራሪው ኃይል የሚሰፈር ቀለብ አነሰኝ በሎ እንደሆነ ያለምንም ርሂራሄ የአካባቢውን ህዝብ ጎተራ ቀዶ የሚበቃውን ይወስዳል፡፡… አርሶ አደሩ ተደፈርኩ ብሎ ከተናገረም መከራው ብዙ ነው፤ ሰበብ አስባብ ፈልገው እስር ቤት ይጣሉትና ከምስቱ ጋር ይተኛሉ…. ወራሪው ኃይል የአካባቢውን ህዝብና መሬት ተከፋፈሎ የሚታረሰውና ጎተራ የሚሰራው በወራሪ ደጅ ሆነ…የተወረሩ ወንዶች አርሶላቸው ሴቶች ደግሞ ፈጭቶላቸው የሚበላው ወራሪው ኃይል ሆነ….. ” መንግስቱ ኃ/ማሪያም
ከላይ የተገለጸው እጅግ ዘግናኝ ድረጊት አገላለጽ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም “ትግላችን” በሚል ርዕስ ከፃፉት መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ ይህንን አገላለጽ የዛሬ መጣጥፌ መግቢያ አድርገ የወሰድኩትም እንድሁ ያለፈውን ብቻ ደጋግመ እያስታወስኩኝ ለመቀየት አይደለም፡፡ ይልቁንም የወራሪ ኃይል አጅንዳ አሁን ባለንበት ወቅት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የወረራው ፍጥነት ከቀድሞ ወረራ ፍጥነት አንጻር እንዴት ይታያል? የመውረሪያ መሳሪያዎችስ ምንደር ናቸው? ለውጥስ? በሚሉ ኃሳቦች ላይ በጥቅሉ አንዳድ ነገር ለማለት ስለፈለኩኝ ነው፡፡
እንደምታውቀው የብሔሮች ጭቆና ጉዳይ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ጉዳይ ነው፡፡ በየጊዜው ሀገርቷን የሚቆጣጠሩ ኃይሎች ብሔሮችን በጭቆና ቀንበር ስር ላማቆየት የተለያየ ስልቶችን እንደሚጠቀሙ የአደባባይ ምስጥር ነው፡፡ ከላይ ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም መጽሐፍ ላይ የተወሰደው ጽሑፍ እንደሚያሳየው በወቅቱ የነበሩ ወራሪዎች ነባርና የአካባቢውን ህዝቦች በግዞት ቀምበር ስር ለማቆየት ክብራቸውን ነጠቁ፤ በባርነት ገዝተዋቸው የራሳቸው ቤት የሚያሞቁ ሎሌዎች ለማድረግ ሌተ ቀን ሰሩ፡፡ ይባስ ብሎም የሀገር ህሊውና ዋስትና የነባር ህዝቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ማንነትና ትውፍት ሲጠፋ ነው ብሎ ከድምዳሜ ደረሱና የተወረሩትን መጤ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት እንዲቀበሉና የራሳቸውን እንዲተው በከፍተኛ ገዥ መደቦችና ወረራውን ተከትሎ በመጡ ኃይማኖት አባቶችና ተከታዮቻቸውም ጭምር ተሰራ፡፡ ድርጊቱን ሊቋቋም የሚሞክር ግለሰብም ሆን ቡድን ከነባሩ ብሔሮች መካከል ከታየ በታጠቁ ወታደሮች በኃይል እንዲደመሰሱ ተደረገ፡፡ 
በሌላ በኩል የራሳቸው ባህል፣ ቋንቋና ትውፊት የኋላ ቀርነት ምልክት እንደሆነ ተደርገው ነጋሪት ተጎሰመ፤ በውጤቱም የነባር ህዝቦች ማንነት የሚገልጽ ነገር እየደበዘዘ ሄደ፡፡ በተጨማሪም በጭቁን ብሔሮች ቋንቋ ስም መሰየም፣ መጻፍ፣ ማንበብ፣ መናገርና ማበልጸግ በግልጽ የሚነቀፍ ተግባር ሆኖ ሰው በመጤ ባህል እንዲቃኝ ተደርጓል፡፡ ለአብነትም አብዘኛው የአሁኗ ኢትዮጵያ ብሔሮች የልጆቻቸውን ስም በአማርኛ ይሰይማሉ፣ “አብይ ጾም” የጾመ ያርዳል ተብሎ “ኡሱራ የጾመ” እንዳያርድ ከመደረጉም በላይ አራጁና ማረጃው ያልተቀደሰ ነው ተብሎ በአደባባይ ተወገዘ፣ ተከለከለ፡፡ በጥቅሉ የቀድሞ ወራሪ ኃይል የመውረሪያ መሳሪያውን ወታደር፣ እምነትና ባህል አድርጎ ነባር ብሔሮችን ተቀጣጠራቸው፤ እናማ ማንነታቸውን ቀምቶ አልፏል፡፡ አልፏል ያልኩት ቀርቷል ቢሆን ምነኛ ደስ ባለኝ፡፡ ምክንያቱም ያለፈው ቢቀር ኖሮ ተጨቁነው የነበሩ፤ ቋንቋቸው፣ ማንነታቸውና ትውፍታቸው ተንቀው የነበሩ ብሔሮች በዘመናዊ መንገድ ባልቀጠለና ባልከፋ ነበር፡፡
ወረራ በዘመነ ኢህአዴግ
================
ከላይ ከኮሎኔል መንግስቱ መጽሐፍ የተወሰዱ ነጥቦች ያሳዩት ድርጊቶች በምንልክ የልጅ ልጆችም ቀጥታ ስራ ላይ እየዋሉ እራሱን ንጉሳዊ ስርዓት ብሎ የሰየመው ስርዓት በ“ያ ትውል” ተንኮታኩቶ ከወደቀና በመኮኒኖች ስብስብ እስከተቀማ ድረስ ቀጥሎ እንደ ነበር ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡
“ያ ትውል” ጭቁንን ብሄሮች ከጎናቸው በማሰለፍ ያመጡት የሌውጥ ምልክት “መሬት ለአራሹ” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ በአንጻሩ መልሶ ሌላውን የህዝብ ጥያቄ ውጦ ቀረ፤ ትግልም ቀጠለ… ደርግም በብሔራዊ ጭቆና ተማረው ነፍጥ በማንሳት ጫካ በገቡ ኃይሎች ግባዓተ መሬቱ ተፈጸመ፡፡ ሌሎችን የነጻነት ኃይሎችን የእሳት ራት አድርጎ ኢህአዴግ እራሱን በስልጣን ኮርቻ ላይ አደረገ…. የመቆጣጠሪያ ልጓምም መቔሌ ገባ፡፡… ጊዜው ይሮጣል፤ ስልጣኔና የአዓለም ዘመናዊነትም ይፈጥናል፡፡
በዜመነ ኢህአዴግ የወራረው መልክና ፍጥነት እጅግ አስከፊ ሆኗል፡፡ ሰርዓቱ ገና የአራት ኪሎን ቤተ መንግስት ከገባ ጀምሮ ለራሱ እድሜ ማራዘሚያ የሚሆኑ ህጎችን፣ መመሪያዎችንና የስለላ መረቦችን መዘርጋት የተያያዘው ውጥን ሰምሮለት ከ1993ዓ.ም ጀምሮ በተለየ ሁኔታ በከተማ መተዳደሪያ ህጎች ላይ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግና በህገ-መንግስቱ ለራሱ ከለያቸው መብቶች መካከል “መሬት የመንግስት ነው” የሚለውን አጀንዳ ተግባራዊ ማድረጉን ተያያዘው፡፡ በዚህም ምክንያት ከተሞች በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት(አደጉ አላልኩም) ተያየዙ፡፡ እንደ ሀዋሳ ያሉ በተፈጥሮ ለመስፋፋትና ለመቀራመት አመች የሆኑ ከተሞች ከፍተኛ የመስፋፋት አጀንዳ ከተያዘባቸው ከተሞች መካከል ዋነኞች ሆኑ፡፡ በከተማ አካባቢ ያለውን ሰፋፊ የአርሶ አደር እርሻ ለመቀራመት የተለያዩ ህጎች (የሊዝ አዋጅን ልብ ይሏል) ወጡ፡፡ በነዚህ ህጎች መሠረት ተወዳድረው ማሸነፍ ያቃተው የአካባቢውና የመሬት ባለቤት የሆነው ህዝብ መሬቱን ለመንግስትና ለደላሎች በእርካሽ ዋጋ ተገዶ እያስረከበ ወደ ዳር ሲገፋ በአንጻሩ ደግሞ በስርዓቱ ባለሀብት የሆኑና በታርክ አጋጣሚ የሀብት ባለቤት የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥርታቸውን ቋጥረው እርካሹን ለመሸመት ወደ ሀዋሳና መሰል ከተሞች ገቡ፤ ገዙ፤ አዲስ መንደር መሰረቱ፡፡ አንዲስ መንደር መመስረቱን ተከትሎ በእርሻና በእርቢ እጅ ወደ አፍ ኑሮ ይገፉ የነበሩና ገንዘብ የሌላቸው ነባር የአካባቢው ህዝቦች ያለ መሬት፣ ያለ ቤትና ንብረት ከመቅረታቸውም በላይ ምስቶች ሴተኛ አዳሪ፣ ባሎች ላብ አደሮች፣ “እድለኛ” የሆኑ የተፈናቃዮች ልጆች ተምረው ለህዝባቸው እንደመድረስ የቅንጡ ቤተሰቦች ልጆች ጠባቂና ከአቅማቸው በላይ የሆነ ስራ የሚሰሩ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ጎዳና ተዳዳሪ ሆኑና መጤዎቹ አዲስ መንደር መስራቾች ተቀምጠው ተመጋቢና ሊጆቻቸው ተረጋግተው ተማሪ ሆኑላቸው፡፡ ነጌ ያልተማሩ የተፈናቃይ ልጆችን ይገዛሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል አዲስ መንደር የመሰረቱት ይዘው የመጡትን በህልና ቋንቋቸውን ማስፋፋት ሲያያዙት በአንጻሩ ደግሞ የነባር ህዝቦች ባህልና ቋንቋ እየከሰመ ሄደ፡፡በቋንቋቻ መማር የለም፣ መጻፍ የለም፣ መዳኘት የለም፡፡ አሁን በደረሰንበት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ትውልድ ከአባቱና እናቱ ውጭ የዘር ግንዱን እንኳን የማያውቅበት ደረጃ ከመድረሳችንም በላይ የመጤ ባህልና ቋንቋ አቀንቃኝና አድናቂ ሆኗል፡፡ ቤተ እምነቶችና የከተማ ህይወትም በጽናት የሚከውኑት ይህንን ነው፡፡ ትላንት በአካባቢው ቋንቋ ሲሰጥ የነበረው በሁሉም ቦታ በሌላ ተተክተዋል፡፡
ለዚህ ውድቄት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደግሞ የዜመኑ ስልጣነን ተከትሎ የመጣው የህዝብ ጊኑኝነት፣ የአካባቢው ገዢዎች የነባሩን ስርዓት የወራራ አጀንዳ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እያስቀጠሉ የራሳቸውን እንዲሞት ማድረጋቸው፣ ጭቁኑ የአካባቢው ብሔር ተወላጅም በከፍተኛ የስለላ መረብ ስር መውደቁና በአንዲነት(በአንድ አጀንዳ ስር) ተንቀሳቅሰው የራሳቸውን ማንነት ለማስከበር ያለው የዓለማ ጽናት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣትና ወ.ዘ.ተ ናቸው፡፡
የሚዲያ ወረራ
=========
ቀደም ባሉት በንጉሶች ወረራ ጊዜያት የወረራው የሚካሄደው በአመትት አንድ ጊዜ ፈረስ ቀልቦ፣ መሳሪያ ወልውሎ ብቻ ጊዜ ወስዶ ነበር የሚካሄደው፡፡ ከቆይታ በኋላ አካባቢውን ወረው ቤተክርስቲያናቸውን ተክለው በቤተክረስቲያን በኩል በንጉሱ ፊቃድ ጊዜ ወስደው ቋንቋቸውንና ባህላቸውን አስገድደው ስለሚያስተምሩ የተወረሩ ብሔሮች ትግል ታክሎበት የመውረሪያ ፍጥነት እጅግ አናሳ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ የአለም ስልጣኔንና የገዢውች ተመሳሳይ የጭቆና አጀንዳ ተጨመሮበት የመወረር ፍጥነት እጅግ በጣም ፈጣን ሆኗል፡፡ ይህንን ፍጥነት ካሳለጡት መሣሪያዎች መካከል ሚዲያ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳል፡፡ የአሁኑ ገዥዎችም ለቀድሞ ወራሪ ኃይል ቋንቋና ባህል መስፋፋት ልዩና ቀጥተኛ ያልሆነ ትኩረት እንደሰጡ ቀጥለዋል፡፡ የሚዲያ አማራጭም እጅግ እየሰፋ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሲደመሩ ለወረራው ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ስለዚህ በየቀኑ ከአብዘኛው (በተለይም ከገዠዎች ሚዲያ) የሚሰማው የወራሪዎች ጀብድ እንጂ የተጨቋኞች ጭቆና አይደለም፡፡ ስለሚኒሊክ አንጂ ስለባልቻ ዎራዎ አይደለም፣ ስለቴዎድሮስ እንጂ ስለ ፊሳ ፊቾ፣ ተክሉ ዮታ፣ ባራንባራስ ሮዳ ፣ መንግሰቱና ወ.ዘ.ተ አይደለም፡፡ እንዲህና እንዲህ ኢያለ ወረራው ዘርፈ ብዙ በሆነ መንገድ በከፍተኛ ፍጥነት ቀጥለዋል፡፡
ከቀደሞ የአሁኑ ባሰ
=============
የቀድሞ ወረራ ለአሁን ውድቀትና ጥፋት ጠንካራ መሰረት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ የብሔር ግንባታ በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ እምነትና ባህል ይረጋገጣል ብሎ ማስተማርና በቀለም ከትቦ ለትውል ማውረስም ስህተት ከመሆኑም ባሻገር ዘር የማጥፊያ ፈንጂ ነው፡፡ ይህንን የአባቶቻቸውን ፍንጂ እርሾ ከዘመናዊነትና ከአሁኑ ገዢዎች ተመሳሳይ ግን የጠለየ ስልት ያለው የወረራ አጀንዳ ተጨማምረውበት ክፋቱ ጨምረዋል፤ በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ፣ በየቀኑ፣ በየሳምነቱ፣ በወሩና በየአመቱ እየተወረረን እንገኛለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የተወራሪዎች አንዲነት፣ መተሳሰብ፣ የትግል ጽናትና መደራጀት እጅግ አናሳ መሆኑ ለወረራው እጅ አዙር አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ቸር ጊዜ!!