Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

አቅጣጫ ሆኖ የከረመውን የደቡብ ክልልን ̈ሕዝባዊ ክልል ፟ አድርጎ መልሶ የማዋቀር ፕሮጄክት

ከአፄ_ምንሊክ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ የነበሩ መንግስታት በሙሉ አሃዳዊ መንግስትን (Unitary Government System) በኢትዮጵያ ገንብተው ጭቆናን ፣ በደልን ፣ ዝርፊያን ፣ ኢ_ፍትሀዊ የሆኑ አሰራሮችን እና ለዜጎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶችን ከማሰፋፋት ውጭ በሀገሪቱ ልማትን ፣ ዕድገትን ፣ ሰላምን ፣ ፍትሀዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እና እኩልነትን ፈጽመው ሊያረጋግጡ አልቻሉም ። በመሆኑም መንግስታቱ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበራቸው በጭንቀት ተወልደው በጭንቀት ከስመዋል ። እነዚህ አሀዳዊ መንግስታት (Unitary Governments) ዛሬ መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም (Geographical Based Federalism System) ተብሎ ከሚቀነቀነው ጋር አንድና አንድ ናቸው ። ስለሆነም በኢትዮጵያ ምድር ላይ እውነተኛ የሆነ ዲሞክራሲ ፣ መልካም አስተዳደር ፣ ፍትህና የዜጎችን እኩልነት ለማረጋገጥ መልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም (Geographical Based Federalism System) ተፈትኖ የወደቀና ምንም ፋይዳ የሌለው እሳቤ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል ።

በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን ድረስ በመንግስት ላይ የቆየውና አሁን እየከሰመ ያለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንፈስ/ጽንሰ_ሀሳብ የሰከረው የወያኔ_ኢህአዴግ መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የህዝብ ፌዴራሊዝምን (Peoples/Ethnic Based Federalism System) እና የመልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝምን (Geographical Based Federalism System) በጣምራ ተግባራዊ አድርጓል ። ይሁን እንጂ ልክ እንደቀድሞዎቹ መንግስታት በኢትዮጵያውን ላይ ግድያን ፣ ግፍን ፣ ጭቆናን ፣ በደልን ፣ ዝርፊያን ፣ ኢ_ፍትሀዊ የሆኑ አሰራሮችን እና ለዜጎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶችን በእጥፍ ከማሰፋፋቱ ውጭ በሀገሪቱ ልማትን ፣ ዕድገትን ፣ ሰላምን ፣ ፍትሀዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እና እኩልነትን ፈጽሞ ሊያረጋግጥ አልቻለም ። ወያኔ ምንም እንኳ ጥምር ሞዴልን በንድፈ_ሀሳብ ደረጃ በወረቀት ላይ ቢያስቀመጥም በተግባር ላይ ሲያውል የከረመው የአሀዳዊ መንግስት ሞዴል (Unitary Government System) ከህወሃት ወገን ብቻ ከላይ ወደታች በሚሰጥ ትዕዛዝ የሚፈጸም በመሆኑ ምክንያት የወያኔ_ኢህአዴግ መንግስት በትረ ስልጣኑን ከጨበጠበት ማግስት ጀምሮ የለየለት ፍጹም አምባገነናዊና ጨካኝ እየሆነ መሄዱ ለማንም ግልጽ ነው ። ከዚህም የተነሳ ከ27 ዓመት ጉዞ በኋላ ለህወሃት ምድር ሲኦል ስለሆነችበት የመግለጫዎች ጋጋታ ፣ ሁከትና ግጭት እየፈበረከ ሰሚ የሌለውን ጩኸት ልክ እንደታረደ በሬ ዓይነት ጩኸት በማሰማት ላይ ይገኛል ። በ43 ዓመት ጉዞው የበደለው መላ የትግራይ ህዝብም ከእንግዲህ ወዲያ ዋስትናና መሸሸጊያ ልሆንለት ፈጽሞ አይችልም ። ምክንያቱም ወያኔ ለዘራው ግፍና በድል ብቻው የእጁን ፍሬ አጭዶ ሊበላ እና ለሌሎች በጭካኔ ያጠጣውን መራራ ጽዋ ብቻውን ሊጠጣ ተራ ደርሶበታልና ። በዚህ ውስጥ ጻድቅ ፈራጂ የሆነው የእግዚአብሔር ቅን ፍርድና ጠንካራ እጅ እንዳለበት ጥርጥር የለውም ።

ወደ ፍሬ ሀሳቡ ልመልሳችሁና በመጀመሪያ ደረጃ ራሳቸውን የኢትዮጵያ ̈ምሁራን ፣ የሥነ_ምርምር ባለሙያዎች ፣ ጋዜጠኞች ወይም ፖለቲከኞች ̈ ነን ብለው ለሚጠሩ ለመልክዓ ምድራዊ ፌዴራሊዝም (Geographical Based Federalism System) አቀንቃኞች በሙሉ አንድ ጥያቄ መሰንዘር እፈልጋለሁ ። በውኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰሜን የሚባል ብሄር/ህዝብ ይኖራል ወይ ? ወይንስ ምስራቅ ወይም ምዕራብ የሚባል ህዝብ ? ወይንም በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሄሮችና ህዝቦች ይኖራሉ ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ ወይንስ በጭራሽ የለም ነው የምትሉት ? መልሳችሁ በዓዕምሮ ደረጃ እና በአፍ ደረጃ የተለያየ መሆኑ አያስገርምም ። በአዕምሮ ደረጃ ከ80 በላይ ብሄሮችና ህዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ ። ነገር ግን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አብረው መኖር ከጀመሩበት ዕለት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በምድር ላይ ያለውን ሀቅ ክዳችሁ ፤ ሌሎችም እንዲክዱ ትሰብካላችሁ /ታሳምናላችሁ ። ምክንያቱም ያለመታደል ሆኖ ፍትህንና እውነትን ማስቀደም ባህላችን ሆኖ ስለማናውቅ ነው ፤ የራስ ጥቅም ስለምናስቀድም የብዙሃኑ ተጠቃሚነት ጉዳያችን ስለማይሆን በእውነት ላይ ለመዋሸት ልባችንን/ህሊናችንን በግድ እናሳምናለን ። በዚህ ደረጃ ላይ ስንደርስ የዕድሜ ትልቅነት ፣የትምህርት ደረጃችን ፣ ሃማኖተኛነት ወዘተ እንዳይሰሩ አድርገን የልባችንን በሮች እንዘጋለን ። ስለዚህ በእውነት ላይ እየዋሸን በእጃችን ላይ የመኪና ቁልፍ ይዘን የቤታችንን በር ለመክፈት እንደምንታገል ሁሉ እንዲሁ ለሀገራችን ችግሮች መፍቻ ያልሆኑ ቁልፎችን ተሸክመን ዘመናችንን በሙሉ እንጓዛለን ። በጣም ያሳዝናል ። መፍትሔው ግን እውነተኛ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነበት ህዝባዊ ፌዴራሊዝም (Peoples/Ethnic Based Federalism System) በመገንባት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በህዝቦቿ እና በህግ የበላይነት ማስከበር ነው ።

የእነመለስና የህወሃት ቡድን በሙሉ መሰረታዊ ስህተታቸው የአሀዳዊና ፌዴራላዊ ጥምር ሞዴል ለኢትዮጵያ ህዝብ እኩልነትና ለሀገር ሉዓላዊነት አደጋ መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው ። ለምሳሌ ያህል ፦ በተፈጥሮአዊ አሰራር ፈረስና አህያ ስዳቀሉ በቅሎን ይወልዳሉ ። ፈረስ ወይም አህያ ከአምሳያቸው ጋር መራባት ስችሉ በቅሎ ግን ዘር የላትም ። በተመሳሳይ መልኩ ባንድ ሀገር ውስጥ አሀዳዊ ሥርዓትና ፌዴራላዊ ሥርዓት በጣምራ በአሀዳዊ አሰራር ሲተገበር ውጤቱ ልክ እንደበቅሎ መካን ፖለቲካ ወይም ፖለቲከኞች ይፈጠርና ለህዝብና ለሀገር ሉዓላዊነት ጠንቅ መሆን እንደሚችል ከ27 ዓመት የወያኔ ጉዞ ለመማር ችለናል ። የተገኘውም ውጤት ህዝብንና ሀገርን ከማልማትና ከመገንባት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማሳደድ ሀገርን ማፍረስና ህዝቦቿን አደጋ/ስጋት ላይ መጣል ነው ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከመኖር ደረጃ ላይ አልፈው ወደ ቡቱቶነት ደረጃ ላይ የደረሱ የህወሃት መሪዎች ባይኔኩላር መነጽር እንኳ ተገጥሞላቸው አጥርተው ማየት በማይችሉበት ደረጃ በናፍቆተ_ንዋይ በሽታ ስለተለከፉ ብቻ ከዶ/ር አብይ መመጣት ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ብቅ ያለውን የሰላም ተስፋና የተገኘውን ለውጥ ለማደናቀፍ ወደ ዋሻቸው ውስጥ ገብተው ስደነፉ እናያቸዋለን ።

በተመሳሳይ መልኩ አሀዳዊ መዋቅራቸውን 56 ብሄሮችን ባንድ ላይ ጨፍልቀው እንድተገብሩላቸው በወያኔ የተጠፈጠፉት እነሀይለማሪም ደሳለኝ ፣ ሽፈራው ሽጉጤ እና ካድሬዎቻቸው ልክ እንደ ዐይናቸው የተንሸዋረረ አመለካከት ያላቸው በመሆናቸው ባሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና የህዝቦች ፍላጎት ምን እንደሆነ ፈጽሞ ሊገባቸው አልቻለም ። በኦቦ ለማ መገርሳ ቲም ውስጥ ከቄሮ የአቅም ግንባታ ስልጠና የወሰደው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ የሊብራሊዝምን ዜማ በሚያቀነቅንበት በዚህ በለውጥ ሂደት ጎዳና ውስጥ ገና ያልነጋለት የሽፈራ ሽጉጤና የሀይለማሪያም ደሳለኝ ርስት የሆነው የደኢህዲን ካምፕ ገና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፊዴል ገበታን ቆጥረው መጨረስ ስላቃታቸው የሲዳማ ኤጄቶ እና የጉራጌ ዘርማ ከቄሮ የተማሩትን ትምህርት ተጠቅመው እየረዱአቸውና በቃችሁ አሁን እረፉ እያሏቸው ይገኛሉ ። ቄሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እውነተኛ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ፌዴራሊዝም (Peoples/Ethnic Based Federalism System) እና ሉዓላዊት ሀገር በመገንባት ረገድ የከፈለው መስዋዕትነትና ያበረከተው አስተምህሮ እጅግ በጣም ታላቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ስልጣን በመያዝ ረገድ ውጤታማም ነው ለማለት ያስችላል።

ቄሮ ቲም ለማን አሰልጥኖ የኦሮሞን ህዝብ ነጻ ማውጣቱን አስተውሎ የተመለከተውና ትምህርት የቀሰመው ፋኖ ደግሞ የጌዱንና የምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀን መኮንን ቲም አሰልጥኖ የአማራን ህዝብ ነጻ የማውጣት ጉዞ አጠናቋል ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በቲም ጌዱ ድጋፍ በቅርቡ የተመሰረተው አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ነው ። ይህም የሚያመለክተው ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች ማንነትና እኩልነት ዋስትና የሚሆነው እውነተኛ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ፌዴራሊዝም ስርዓት (Peoples/Ethnic Based Federalism System) ከሀገር ሉዓላዊነትና ዜጎች መብት መከባበር ጋር በተዛመደ ቅኝት ሲተገበር ብቻ መሆኑን ነው ። በሌላ በኩል ይህ የሚያሳየን ደግሞ ባለፉት መንግስታት የተሞከረው የአሀዳዊ መንግስት አሰራር (Unitary Government System or Geographical Based Federalism System) ተፈትኖ ውድቅ እንደሆነ ሁሉ ፤ ባለፉት 27 ዓመታት ህወሃት ሲተገብረው የኖረ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት መርሆ/ሞዴል ማለትም የአሀዳዊና ፌዴራሊዝም ጥምር መርሆ/ሞዴል (Unitary Government System and Geographical Based Federalism System) ተፈትኖ የወደቀ መሆኑና ልክ እንደበቅሎዋ መካን መሆኑ ከረጅም ሂደት በሚገባ ተረጋግጧል ። ልክ እንደአባቱ ህወሃት የወደቀውን ሞዴል በ56 ብሄሮች ጫንቃ ላይ አሸክሞ ዞር አልል ብሎ በለውጡ ግስጋሴ ጎዳና ላይ ደንቃራና እንቅፋት ሆኖ እያስቸገረ ያለውን የደኢህዲን ምሽግ ከነመሰረቱ ለመናድ የሲዳማ ኤጄቶና የጉራጌ ዘርማ እያደረጉት ላለው ብርቱ ትግል ቄሮና ፋኖ ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን እንድያደርጉና ልምዳቸውንም እንድያካፍሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ።

ባንድ እራስ ላይ በከፍል የተላጨ በከፍል ደግሞ አፍሮ የተበጠረ ፀጉር ውበት እንደለሌው ሁሉ ፤ 56 ብሄሮች ማንነትን በማይገልጽ ደቡብ ተብሎ በህወሃትና በተላላኪዎቻቸው አማካይነት በአቅጣጫ በተሰየመበትና በደኢህዲን ልዩ ጥበቃ ተጠፍሮ በታሰረበትና ነጻ ባልወጡበት ሁኔታ ውስጥ የናንተ ብቻ ነጻ መውጣት ለእውነተኛ ዲሞክራሲና ፍትህ መስፈን በቂ ዋስትና ሊሆን አይችልም ። በተመሳሳይ መልኩ የክልል ከተሞችን ተጣድፎ በፌዴራል መንግስት ስልጣን ስር ለማስገባት የሚደረግ ሩጫም ብቻውን ሀገሪቱን ከአደጋ ሊታደግ አይችልም ። ይልቁንም በህዝብና በመንግስት መካከል የሚኖረውን አመኔታ በይበልጥ እየሸረሸረ ለዶ/ር አብይ መንግስት ለነገ የመሰናክል ድንጋይ ያስቀምጥ ይሆናል እንጂ ። የሀዋሳ ከተማን የፌዴራል ለማድረግ እነሀይለማሪያምና ደኢህዲን ካድሬዎች በሙሉ የሚያደርጉት ሽር ጉድ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት እንቅፋት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ቢወስድ እንጂ ያለህዝቡ ይሁኝታ የሲዳማን ህዝብ አፍ በስልጣንና በጠብመንጃ ሀይል አስዘግተውና አስፈራርተው የነጠቁት መሬት እስከ ጥቁር ውሃ ድረስ ያለው በሙሉ ባንድ ቀን በሲዳማ ኤጄቶዎች ትግል የሚመለስና ከተማውም አንድ ቀን እንደሄሮሽማና ነጋሳኪ በእሳት እንደሚጋይ ለማንም ስጋት ልገባው አይገባም ። ያሁኗ ትንሿ ብልጭታ ምናልባትም ለዶ/ር አብይ መንግስት ጥሩ ምልክትና ትምህርት ትሰጣለች ብዬ እገምታለሁ ። ̈እግዚአብሄር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል ፟ ይላል መጽሀፍ ቅዱስ ። የሲዳማ ህዝብ እግዚአብሄርን ያምናል ፤ ይታመንበታልም ።ጥናቶች እንደሚያመለክቱት 96 በመቶ የሚሆን የሲዳማ ህዝብ በሙሉ ክርስቲያን ነው ። ምናልባትም ዛሬ ሲዳማን የሚያስጨንቁና እያሳደዱ ያሉ የደኢህዲን ካድሬዎች በሙሉ ቀደም ሲል ወላጆቻቸው ወንጌልን ይዘው በሲዳማ ምድር የሰበኩ ልጆች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ ። ትውልድ የወንጌልን ትርጉም በተሳሳተ መልኩ በተግባር እያየ ስለሆነ ነገ ለማንም የማይበጁ ክስተቶች ብቅ ማለታቸው የማይቀር ይሆናል ።

ስለሆነም ወያኔ_ደኢህዲን በሰላም በኖሩ ህዝቦች መካከል ሁከት ለመፍጠር በተለይም የሀዋሳን ከተማ ከሲዳማ ህዝብ እጅ ለመንጠቅ በፌዴራልነት ሰበብ የሚያደርገው ሩጫ ነገ ለሀገር የሚተርፍ ሰደድ እሳት አዳፍኖ የማቆየት አዝማሚያ ያለው መሆኑን በመረዳት ከቄሮና ከፋኖ ድጋፍ በተጨማሪ ቲም ለማና ቲም ጌዱ የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይን ራዕይ በመደገፍ በቆሙበት መስመር የሲዳማ ህዝብን እሮሮ በመጋራት አሁን የተገኘው ለውጥ በሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር እንዲደርስና በህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምና የወንድማማችነት መንፈስ እውን እንዲሆን ስባል ከተሞችን ከመሻማት በፊት ሀገሪቱን መልሶ የማዋቀር ስራ ትኩረት የሚገባው ጉዳይ መሆኑ ማሳሰብ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ ። የኢትዮጵያ ህገ_መንግስት ብሄሮችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንድያስተዳድሩ የሚፈቅድ በመሆኑ ህወሃት_ኢህአዴግ ሲከተል የነበረውን የተሳሳተ አሀዳዊና ፌዴራሊዝም ስርዓት ጣምራ ሞዴል የአሀዳዊውን ስርዓት ክንፍ በመስበር እውነተኛ ፌዴራሊዝም ስርዓት ማሳደግ ወሳኝ ይሆናል ። በአሰራር ደረጃ አሀዳዊው ስርዓት በመላ ሀገሪቱ ላይ የተተገበረው በህወሃት የበላይነት ሲሆን በመዋቅር ደረጃ የተተገበረው ግን 56 ብሄሮችን ባንድ ላይ በያዘ በደቡብ ክልል ውስጥ ነው ።

ይህ ተፈትኖ የወደቀው አሀዳዊ አገዛዝ ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የደኢህዲን ካድሬዎችን እንደፈረስ ከማድለቡ ውጭ ለህዝቡ ያተረፈው ነገር ቢኖር ፍጽም የሆነ ድህነትና በማንነቱ ኮርቶ ባገሩ እንዳይኖር በካድሬዎቹ የምደረግ ወከባ ፣ እንግልት ፣ የፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ብቻ ነው ። እነዚህን በርካታ ብሄሮችን ባንድ ክልልነት ለማዋቀር የሚያስችል ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ የሆነ ትንታኔና መስፈርትም አይኖርም ። 56ቱ ብሄሮች በኩሽ ፣ በሰም እና በኦሞ የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ የምመደቡ እንዲሁም የራሳቸው የሆነ ታሪክ ፣ ባህል ፣ ቋንቋና የመሬት ይዞታ ያላቸው ናቸው ። ስለዚህ ስህተቱ አማርኛ ብቻ የነርሱ አስተዳደር ክልል የስራ ቋንቋ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አንድ አርሶ/አርብቶ አደር ፍትህ ፍለጋ ከማጂ ፣ ከቤንች ፣ ከካፋ ፣ ከዳውሮ ፣ ከደቡብ ኦሞ ፣ ከጋሞ ፣ ከጎፋ ፣ ከኮንሶ ፣ ከቡርጂ ወይም ከሌላ ዞን ተነስቶ ከሩቅ ወደ ሀዋሳ እንዲመጣ ማድረግ በራሱ የፍትህ ሚዛን ጉድለት መኖሩን እና መልካም አስተዳደር በአገር ውስጥ ጨርሶ የሌለ መሆኑን ያመለክታል ። ስለዚህ የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ መንግስት ከቲም ለማና ጌዱ ጋር ተቀናጅቶ ደቡብ የተባለውን ክልል እንደገና በህዝባዊ መሰረቶች ላይ መልሶ በማዋቀር ለህዝቡ ሰቆቃ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል ። ደኢህዲን የወያኔ/ህወሃት ሁለተኛ ምሽግ ስለሆነ በአገሪቱ ውስጥ እየተደረገ ላለው ለውጥ እንቅፋት መሆኑንም ብዙዎች ያምኑበታል ።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ውስጥ ከ86 የማያንሱ ብሄሮች/ብሄረሰቦች እና ከ100 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ እንደሚኖር እሙን ነው ። እያንዳንዱ ብሄር የራሱ የሆነ መጠሪያ ስም ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ ፣ ባህልና አሰፋፈር አለው ። ሰሜን የሚባል ብሄር ወይም ህዝብ እንደሌለ ሁሉ ደቡብ የሚባል ብሄር ወይም ህዝብ የለም ፤ በተመሳሳይ መልኩ ምስራቅ የሚባል ብሄር/ህዝብ እንደሌለ ሁሉ ምዕራብ የሚባል ብሄር/ህዝብ የለም ። ህዝቦች በማንነታቸው ይገለጻሉ እንጂ በአቅጣጫ ፈጽሞ አይገለጹም ። ስለሆነም ደቡብ የሚባለውን የህወሃት የፈጠራ ክልልና የተደራጀ ሌብነት ምሽግ የሆነውን አፍርሶ በምትኩ ስድስት በማንነት ላይ የተመሰረቱና ህዝባዊ መሰረት ያላቸውን ክልሎች ማዋቀር ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፣ ለዘላቂ ሰላም እና ለፍትህና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ሚቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ብዬ እገምታለሁ ። ለዚህ ጥናት ፕሮፖዛል መደሚደሚያ ታሳቢ የሆነው እስካሁን ድረስ ማንነትን መሰረት አድርገው የተደራጁና በስራ ላይ ያሉ ክልሎች መዋቅር ሲሆን እነርሱም የኦሮሞ ብሄራዊ ክልል ፣ የአማራ ብሄራዊ ክልል ፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልል ፣ የአፋር ብሄራዊ ክልል ፣የሶማሌ ብሄራዊ ክልል ፣ የሀረሪ ብሄራዊ ክልል ፣ የቤኒሻንጉል ብሄራዊ ክልል እና የጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ናቸው ። ለምሳሌ ያህል ከነዚህ ክልሎች መካከል ከ40 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለው የኦሮሞ ብሄራዊ ክልልም ሆነ 200 ሺህ ያለው የጋምቤላ ብሄራዊ ክልል ወይም 20 ሺህ ህዝብ ያለው የሀረሪ ብሄራዊ ክልል የተዋቀሩት በማንነት ላይ ተመስርተው እንጂ በሌላ አይደሉም ። ታዲያ ከሀረሪ ወይም ከጋምቤላ ክልል የሚያንስ ማን ነው ? ህወሃት ለክልሎች የሰጠው የተዛባና አድሏዊ አሰራር ለሌሎች ክልል የመሆን መብትን ለመንፈግ ዓይነተኛ ምክንያትና መከራከሪያ ሆኖ ፈጽሞ ሊቀርብ አይገባውም ፤ ምክንያቱም የህወሃት በደልና መሴሪነት ባደባባይ ላይ እርቃኑን የተሰጠበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናልና ። በሌላ በኩል ሶስት ወይም አራት ብሄሮች ባንድ ላይ ተጣምረው ስዋቀሩ ስያሜ ሊረዝም ይችላል የሚል ክርክር እንዳይነሳ ድሮም ቢሆን የደቡብ ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሚለው ስያሜ በጣም ረጂም ነው ። ከእንግዲህም ቢሆን ከርሱ የሚረዝም ስያሜ አይመጣም ። ስለሆነም የአዳዲስ ክልሎች ስያሜና ዋና ከተማቸው እንደሚከተለው በሰንጠረዥ ተመልክቷል ።

ሠንጠረዥ 1 ፦ በኢትዮጵያ በተጨማሪነት መዋቀር የሚገባቸው አዳዲስ የክልል አደረጃጀቶች 
ተ/ቁ የክልል ስያሜ ዋና ከተማ
1 ሲዳማ ብሄራዊ ክልል ሀዋሳ
2 ጉራጌ_ስልጤ ብሄራዊ ክልል ወልቂጤ
3 ካፋ_ሻካ_ቤንች_ማጂ ብሄራዊ ክልል ቦንጋ
4 ሀዲያ_ካምታ_ሀላዋ ብሄራዊ ክልል ሆሳና
5 ወላይታ_ኦሞ ብሄራዊ ክልል ሶዶ/አርባ ምንጭ
6 ጌደኦ_ኮሬ_ኮንሶ_ቡርጂ ብሄራዊ ክልል ዲላ