Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማ ህዝብ ህገመንግሥታዊ የመብት ጥያቄ በደህዴን ማስፈራርያና ዛቻ ልቆም አይችልም!


ሰሞኑን የበደቡብ ብሔር ብሔርሰቦችና ህዝቦች ክልል የመንግሥት ግንኙነት ጽህፈት ቤት የሲዳማን ህዝብ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የክልሉ መንግሥት ነን ባዮች ህዝባችንን ምን ያህል እንደሚንቁ ማሳያ ማስረጃ እንደሆነ ማንም መታዘብ ይችላል። የመግለጫው ዋነኛው መልዕክት የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደር ያለውን ፍላጎት ዳግም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ማንሳቱን ማውገዝ ነው።
ይህ ዋነኛ ሀሳብ ከመግለጫው የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ጀምሮ በግልጽ ተቀምጦአል። የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር “ዛሬም ሲዳማ ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ ይቀጥላል” ይላል። በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴማክራሲያዊ መንግሥት የተዋቀሩ ዘጠኙ ክልሎች በውስጣቸው የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች ተወላጆች ከክልሉ ባለቤቶች ጋር አብረው በሠላም፣ በፍቅርና በመከባበር አይኖሩም ለማለት እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የሲዳማ ህዝብ የራሱን ክልል መሥርቶ መኖር ከጀመረ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር አይችልም የሚል መልዕክት በዚህ ወቅት ክልሉ ለምን ማስተላለፍ እንደፈለገ ግልጽ ነው። 
ህወኃትም ሆነ ኢህአዴግ የሚያራሚደው ፖለቲካ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መካከል ጠላትነትን በመፍጠር ነው። ሰለሆነም የሲዳማ ህዝብ የመብት ጥያቄ ወይም የሲዳማ ህዝብ ክልል መሆን በክልሉ ለሚገኙ ለሌሎች ብሄር ተወላጆች ስጋት እንደሆነ መልዕክት በማስተላለፍ ሲዳማን በጠላትነትና በጥርጣሬ እንድታይ ማደረግ ነው። ይህ ደግሞ በደቡብም ሆነ በአገራችን ባሉ ህዝቦች ዘንድ ከቶዉኑ ተቀባይነት የለሌው ከንቱ ልፋት ነው። ምክንያቱም በሲዳማ ዞን ገጠሮችና ከተሞች ባሉ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ በንግድ ዘርፎች፣ በግብርና ወዘተ ተሠማርተው ህዝቡን በማገልገል የሚገኙ ከሲዳማው ተወላጆች ባልተናነሠ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ናቸው። እነዚህ በሲዳማ ዞን ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ብሄር ተወላጆች በታሪክ ተፈናቀልን፣ በማንነታችን ጉዳት ደረሰብን ያሉበት አንዳችም አጋጣሚ የለም። ይልቁን በሌሎች አካባቢወች ጉዳት የደራሰባቸው በሲዳማ ዞን ተጠልለው ይታያሉ እንጂ። የማንነትን የመብት ጥያቄ ከአብሮ መኖር ጋር ማዛመድ ያስፈለገው የህወኃቱ ደህዴን ግን የደቡብ ህዝቦችን ጥያቄ ሲያፍን የኖረበትን ስልት ከማሳየት የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም።
የፖለቲካና የመብት ጥያቄ የሆነውን ራስን በራስ የማስተዳደር የማንነት ጥያቄን ከባህልና ቱሪዝም ጋር በማዛመድ በዞኑ የባህል ተቋም እንድሠጥ የተደረገው መግለጫ የክልል ጥያቄ ማንሳትን ልዩነትን የሚያጎላ፣ የሀገሪቷን እድገት የሚያጓትት፣ የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን በማብራራት ይገልጸዋል። የሲዳማ ክልል መሆን ከአጎራባች ከልልና ዞኖች ጋር እንድሁም በውስጡ ከሚኖሩት ሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በፍቅር በአብሮነት መኖርን የሚያስቀር እንደሆነ የሚገልጸው ማብራርያው ይህን ጥያቄ ማንሳት ብሄሩን ከሌላው ብሄረሰብ ጋር ማጋጨት እንደሆነ፣ የሲዳማን ታሪክ የሚያጎድፍ፣ የጸረ ሠላማ ኃይሎች ወሬ እንደሆነ የገለጸው፣ ዞኑ ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም አሁን ባለው በደቡብ ታቅፎ አብሮ መኖር አማራጭ የሌለው እንደሆነ መግለጫዉ ይገልጻል። የዚህ መግለጫ ዋነኛው ቁልፍ መልዕክት እንደዚ ዓይነት ጥያቄን ማንሳት ፀረ-ሠላም በመሆኑ እርምጃ ስለሚወሰድባችሁ አርፋችሁ ቁጭ በሉ ብሎ የተለመደውንና ጊዜ ያለፈበትን የኢህአዴግን የማስፈራርያ ስልት በመጠቀም ህዝቡን በማስፈራራት የሲዳማን ሕዝብ ጥያቄ ለማፈን እንደሆነ ግልጽ ነው።
ከላይ የተጠቀሰው የመግለጫው ዋና ዋና ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ በጥቅሉ ይህን መግለጫ በዚህ ሰዓት በባህልና ቱሪዚም በኩል እንድወጣ የተፈለገበት ዓላማ እና ለማስተላለፍ የተፈለገው የተሳሳተ መልዕክት እና ቀጣይ ትግላችን ምን መምሰል ይኖርበታል የሚሉትን ነጥቦች ማንሳት ተገብ ይመስለኛል። 
ጠቅላይ ሚንስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ሐዋሳ ተገኝተው ከተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳወች ከተወከሉ ሳይሆን ከተመረጡ፣ እንድሁም ደግሞ በደህዴን አማካኝነት ምን ማንሳት እንዳለባቸው ኦሬንተሺን በወሰዱ የደህዴን አባላቶች የቀረቡ ጥያቄወች የክልሉንም ሆነ የሲዳማን የመብት ጥያቄ ባለማንሳታቸውና ይህንን ጥያቄ ልያቀርቡ የሚችሉ ግለሰቦች በስህተት እንኳን እንዳይገቡ በመደረጉ በሲዳማ ህዝብና በሲዳማ ኤጄቶወች ዘንድ የፈጠረው ቁጣ ይህ ክልል የመሆን ጥያቄ በተገኘው የሚዲያ መድረኮች እንድሁም በቤት ውስጥ፣ በሠፈርና ባጠቃላይ በሲዳማ ተወላጆች ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እንድቀሰቀስ አድርጎአል።
ከላይ የተገለጸው በሲዳማ ኤጄቶወች የተቀሰቀሰው ማዕበል ያስፈራው በህወኃት የሚመራው ደህዴን ለሲዳማ ህዝብ መብት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ህገመንግሥቱን በሚጻረር መልኩ በህገ ደንቡ ላይ በማስቀመጥ የሲዳማ ክልል መሆን ፈጸሞ የማይቻል መሆኑን፣ ሆኖም የሲዳማ ሕዝብ የክልል ጥያቄውን እውን የሚያደርገው በህጋዊና ህገ መንግሥታዊ መንገድ ልሆን እንደማይችል ለማስረዳትም ጭምር ነው። በድጋሚ የሲዳማ ተወለጆች ደም ሳይፈስ ክልል የመሆኑ መብት የማይታሰብ እንደሆነ ይጠቁማል መግለጫው። ህገመንግሥቱን ተከትሎ የክልል ጥያቄ ያነሳውን ብሄር ጸረ-ሠላም ኃይሎች ካለ ቀጣዩ ተግባር የሚሆነው እነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ይህን ኃይል ለመመከትንና የሲዳማን የመብት ጥያቄ ከግብ ለማድረስ የሲዳማ ኤጄቶወች በልዩ ሁኔታ መንቀሳቀስና ከሌሎች ብሄር ተወላጆች ጋር በመሆን መታገል ይኖርባቸዋል።
የሲዳማን ጥያቄ በየደረጃው ለማፈን የህወኃት መሣርያ ሆነው የሚያገለግሉ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች በአገርቷ ያለውን ለውጥ እንደአጋጣሚ በመጠቀም ከኤጄቶወችና ከህዝባቸው ጎን መሠለፍ ይኖርባቸዋል። 
አቶ ጀጎ አገኘሁ የተባሉ ግለሰብ በሲዳማ ዞን የባህልና ቱሪዚም ኃላፊ ያወጡት መግለጫ ምንም አይነት የባሀል ይዘት የለለው የፖለቲካ ጽሁፍ በመንግሥት ሚዲያ ላይ በማቅርብ በድጋሚ በሲዳማ ህዝብ ላይ ክህደት መፈጸሞን እና ከዚህ ቀደም የሲዳማን ህዝብ ለማስጨፍጨፍ ሴራውን ከጀርባ በማሴር ለህዝብ ሳይታዩ ከፊት ለፈት ግን የሲዳማን ተወላጆች በማጋፈጥ ምርጥ የሲዳማን ልጆች ዋጋ ያስከፈሉ መሰሪወች ዛሬም ተመሳሳይ ተንኮል እየፈጸሙ እንደሆነ ተገንዝበው ህዝቡን ይቅርታ እንድጠይቁ፣ ካልሆነ ግን በሲዳማ ህዝብ ላይ ታሪካዊ ስህተት ከሰሩ ግለሰቦች አንዱ እንደሚሆኑና እንደሚጠየቁ ልያውቁ ይገባል።
ከዚህ በፊት ለብሄሩ መብት ይታገሉና ይናገሩ የነበሩ የሲዳማ ምሁራን በሙሉ ከመንግሥት መዋቅር እንድወጡና ተጽኖ እንዳይፈጥሩ በማድረግ እነ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የመሳሰሉ ለህዝብ ሳይሆን ለግል ጥቅምና ለሥልጣን የሚኖሩ ግለሰቦች የሲዳማ ክልል ጉዳይ ለነሱ የግል ሥልጣናቸው ከገዥው ከህወኃት ኢህአዴግ መደራደርያ ካርድ ሆኖ ጠቅሟቸዋል። ሲዳማ ይህንን የክልል ጥያቄ እንዳያነሳ በማፈን የራሳቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ ሹመታቸው እንደሚጠበቅላቸው ካልሆነ ደግሞ በሠሩት ጥፋት ልክ ቅጣት እንደሚገጥማቸው ስለሚነገራቸው ከህዝብ ይልቅ የራሣቸውን ጥቅም በማስቀደም ይኖራሉ። ለዚህ ግልጽ መረጃ አቶ ሽፈራው በሚሾሙበት ወቅት “የክልሉን አንድነት በመጠበቅ” እየተባለ የሚነበብላቸው ታሪካቸው ነው። 
የሲዳማ ሕዝብ መብቱን ለማስጠበቅ ከራሱ በላይ ሌላ ማንም ልኖር እንደማይችል ሕዝቡ ማወቅ መቻል ይኖርበታል። የሕዝብን ጥያቄ አድምጦ ምላሽ መስጠት የኢህአዴግ ባህሪይ እንዳልሆነ ላለፉት 27 ዓመታት አይተናል። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል ህዝቡ የመብት ጥያቄ ስያነሳ ሕዝቡን ማስፈራራት፣ ማሰር፣ መግደል እና ማሰቃየት፤ ከቁጥጥሩ ዉጪ ስሆን ደግሞ ጊዜያዊ ማስታገሻ መስጠት የኢህአዴግ መንግስት ልማዱ ነው። ስለዚህ የሲዳማ ህዝብ ላነሳው ጥያቄ በህገመንግሥታዊ መንገድ ምላሽ ይገኛል ብሎ ማመን ከእውነት የራቀ እንደሆነና የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ የሚመለሰው በራሱ በህዝቡ ብቻ እንደሆነ ልታወቅ ይገባል።
ድል ለጭቁኑ ለሲዳማ ህዝብ