Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

በሲዳማ የማንነት መቃብር ላይ የተመሠረተች “ትንሿ ኢትዮጵያ” ደቡብ

May 26, 2018

በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ቢሔሮች እራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ የሚለው ህገመንግሥታዊ ድንጋጌ ሳይተገበር ሶስት አሥርት ዓመታት ልሞሉት ጥቂት ጊዜያት ቀርቷል። ሆኖም ኢህአዴግ 27ተኛውን የስልጣን ዘመኑን ግንቦት 20 በሚያከብርበት በዚህ ወቅትም እውነታውን ከህዝብ ለመደበቅ ይሞክራል። ይህንን ውሸትም በመቀበል ድርጅቱ የቢሔሮች ቢሔረስቦች መብት ጠበቃ እንደሆነ የሚናገር ህዝብ ቁጥር ቀላል አይደለም ። በኢህአዴግ አገዛዝ  ክልሎችን በብሔር  አሠፋፈር ማዋቀር ቅድሚያ የሚሠጠው ቢሆንም አፈጻጸሙ የሚወሰነው ግን ከህዝቦች ጥቅም አንጻር ሳይሆን ከገዥው መንግሥት የፖለቲካ ጥቅም መጠበቅ ጋር ተያይዞ ነው።  ሟቹ ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ሥልጣን ላይ የሚገኙት  የኢህአዴግ ተላላኪ ሹማሚንቶች የሲዳማን የመደራጀት የመብት ጥያቄ  የሚያፍኑበት ምክንያትን ለራሳቸውም ሆነ  ለህዝቡ የሚያስረዱበት መንገድ የሚያሳየው ይሄንኑ ነው።

ሲዳማ  በክልል ከተዋቀረ ደቡብ ይፈርሳል፣ ደቡብ ከፈረሰ ደኢህዴን ህልውናውን ያጣል። የደኢህዴን ህልውና ከከሰመ ደግሞ ሲዳማም ሆነ ሌሎች የራሳቸውን የፖለቲካ ድርጅት ማዋቀራቸው የግድ ይላል። የሚዋቀረውን አዲሱን ክልል የሚያስተዳድረው ድርጅት ደግሞ  በኢህአዴጋዊ መዋቅር ላይ አዲስ ጫና መፍጠሩ አይቀርም። የኢህአደግ አባል ድርጅት ብሆን እንኩዋን።

በአሁኑ ጊዜ ኢህአደግን ያዋቀሩት የፖለቲካ ድርጅቶች አራት እንደሆኑ ይታወቃል።  የአማራው-ብአዴን፣ የኦሮሚያው-ኦህዴድ፣ የትግራይ-ህወኃት እና የደቡቡ-ደኢህዴን። እነዚህ  ክልሎች በኢህአዴግ አስተሳሰብ ለመመራት ዝግጁ የሆኑ ሲሆን (በራሳቸው አገላለጽ) ሌሎች የተቀሩት ክልሎች ማለትም አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል፣ ሐረሪ እና ጋምቤላ ደግሞ ማህበራዊ መሠረታቸው ከኢህአዴጋውያኑ የሚለይ በመሆኑ ኢህአዴግ አጋሮቼ ናቸው ይላቸዋል።  ልዩነቱ በኢህአዴጋውያን እምነት አጋር ክልሎች በጎሳ አስተዳደራዊ ሥርዓት የሚተዳደሩ በመሆኑ እና አብዛኞቹ አርብቶ አደር በመሆናቸው ኢህአዴግ በያዛቸው ፕሮግራሞች ማዕቀፍ ገብተው ለመተዳደር ዝግጁወች አይደሉም በሚል ነው።

እውነታው ስፈተሽ ግን አሁንም የተባለው ሳይሆን የህወኃት  የፖለቲካ  ስትራቴጂ አካል መሆኑ ነው።  በአንዳች አጋጣሚ አራቱ የኢህአዴግ ክልሎች ከህወኃት ቁጥጥር ውጪ የሚሆኑበት ክስተት ከተፈጠረ እና ጠንካራ ሆነው ህወኃትን የሚፈታተኑ ከሆነ ለህወኃት የፖለቲካ ሚዛኑን እንድያስተካክሉ እንዲሁም ሁሉም በአጋር ድርጅቶች የሚተዳደሩት ክልሎች ከጎሮቤት አገሮች የተዋሰኑ በመሆኑ ህወኃት ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚነሳበትን ኃይል ያለአንዳች የህግ ክልከላ መቆጣጠር እንድችል ታስበው የተተው(ክልሉን የሚመሩ ድርጅቶች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንዳይሆኑ የተደረጉበት ሂደት) ክልሎች ናቸው። ጋምቤላ-ከደቡብ ሱዳን፣ ቤንሻንጉል-ከሱዳን፣ ሶማሌ -ሶከማሊያ፣ አፋር-ከኤርትራ ፣ ሀረሪ-ከሶማሊያ ማዋሰናቸው ልብ ይለዋል።

በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ማዕበሉ በፈጠረው ለውጥ ምክንያት ፍርክስክሱ እየወጣ የሚገኘው አብዮታዊ ዴሞክራስያዊ የህወኃት አገዛዝ የመጣበትን ናዳ ለመቋቋም ለክፉ ቀናት የተዋቸውን የአጋር ድርጅቶችን አጀንዳ በመቅርጽ ለቀጣዩ  ጉባኤ እየተጠባበቀ ይገኛል። አርቆ አላሚው የመሠሪ ፓለቲካ ባለቤቱ ህወኃት አጋር ክልሎችን በኢህአዴግ ማዕቀፍ ሳያስገባቸው ለምን እንዳቆያቸው፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከኢህአዴግ ጋር እንድቀላቀሉ አወንታዊ  ምላሽ  በመስጠት በሌሎች ላይ  ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ  እንደሆነ የሚያስተውሉ ኢህአዴጋውያን ቁጥር ግን ጥቂት ነው።

የሲዳማ ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር ፍላጎት ማፈንም የህወኃት ኢህአዴግ ከፖለቲካ መሰሪ ስልቶች ሌላኛውና  አደገኛው ነው።

ህወኃት ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ  በከፍተኛ  ሁኔታ ከሚጠራጠረውና ከሚፈራው ህዝብ አንዱ የኦሮሞ ህዝብ  ነው። የኦሮሞ ህዝብ በሀብቱም ሆነ  በህዝብ ቁጥር ትልቅ ህዝብ ነው። በተማረ የህዝብ ብዛትም ሆነ  ለሀገሪቷ ከሚያበረክተው የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ  ይገኛል።  በመሆኑም ህወኃት በኤርትራና በሌሎች ድጋፍ ደርግን ከሥልጣን ካስወገደ በኃላ ትልቁ ፈተናውና ፍራቻው ይህ ትልቅ ህዝብ ይውጠኛል የሚል ከፍተኛ  ስጋት ቀዳሚው ትኩርት የሰጠው የፓለቲካ ጉዳይ ነው።

በመሆኑም ይህንን የኦሮሞ ትልቅነት ለመቀነስ እና ከሌሎች ለማመጣጠን የሚያስችለውን ስልት ከመቀየስ አልቦዘነም። ኦሮሚያን ለማሣነስ የቀየሰው ስልት ግን አንድ ብቻ አለነበረም። በዚህኛው ጽሁፍ ትኩረት የተሰጠውን ሀሳብ ብቻ አንስቶ ከማለፍ ግን ሥልቶቹን አንባቢ እንዲያውቃቸው ጠቀስ አድርጎ ማለፍ ተገብ ይሆናል።

ህወኃት ኦሮሚያን በቆዳም ሆነ  በህዝብ ቁጥር ለማሳነስ አንደኛው ስልቱ የኦሮሚያ አካል የነበረችዋን ሀረሪን ራሱን ችሎ  በክልል እንዲዋቀር ማድረግ ነበር። የሀረሪ ህዝብ የራሱ ማንነት  ያለውና  በራሱ የመተዳደር ፍላጎት ያለው  ህዝብ ቢሆንም በክልል እንዲዋቀር የተደረገበት  ዋነኛው ምክንያት ግን ይህንን ፍላጎት መነሻ ያደረገ አልነበረም። በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንድ የጎሮቤት አገር ጋር በማገናኘት ምክንያት የሚሰጡ ወገኖች ቢኖሩም  የህወኃት ዋነኛ ዓላማ ግን ኦሮሞን በቁጥርም ሆነ በቆዳ ማሳነስን ዒላማ ያደረገ ነበር።

ሁለተኛው የህወሀት ስልት ከኦሮሚያ ጋር ሊስተካከል የሚችል ተመጣጣኝ ክልል መፍጠር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የተመረጠው በሽግግር ወቅት በአምስት ክልሎች ተዋቅሮ  የነበረው በአሁን ጊዜ በአቅጣጫ ስያሜ የሚጠራው የደቡብ ክልል ነው። የደቡብ ክልል በውስጡ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈ ክልል ነው። ሁሉም ብሔሮች የራሳቸው ማንነት፣ ስነልቦናና የተለየ ትስስር የፈጠሩ ናቸው። ለብሔር ብሔረሰቦች መብት ቆሜያለሁ የሚለው ገዥው ድርጅት ኢህአዴግ ከልብ እምነት የመነጨ የብሔር ማንነትና መብት መጠበቅ የሚገደው አይደለም። በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ በወሬ ደረጃ የሚናፈሰው የተሳሳተና የተዛባ ትርክት ኢህአዴግ የብሔርሰቦችን መብት በማስከበር ኢትዮጵያዊ አንድነትን ሸርሽሮታል የሚል ሲሆን ይህ ትርክት በከፍል መስተካከል ያለበት ነው። ይሄውም ኢህአዴግ የብሔረሰቦችን መብት ያላስከበረ ከመሆኑም ባሻገር በሚያሳፍርና በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ ማንነት ያላቸውን ብሔሮች ክብራቸውን በሚያዋርድ እና ማንነታቸውን በሚያጠፋ  መልኩ አንድ ቦታ ጨፍልቆ አስቀምጦአቸዋልና።

ይህንን የህወኃትን የፖለቲካ ደባ ከጅምሩ የተረዳው የሲዳማ ህዝብ ኢህአዴግ የጠራውን የሽግግር ወቅት ጉባዔ ረግጦ  መውጣቱ የሚታወስ ነው። ይህ ህዝብ ቀደም ሲል የነበረውን ክልላዊ ስያሜ እንኳን አጥቶም ቢሆን ኢህአዴግ በሂደት ህገ መንግስቱን ይተገብረዋል የሚለውን እምነት በመያዝ በተከታታይ ከማንነቱ ጋር የተያያዘውን ጥያቄ  ሲያቀርብ ሰነባብቷል። በህዝቡ ባህልና  ስነሥርዓት መሠረት ጥያቄውን ሲያቀርብ የቆየው በሠላማዊ መንገድ ከመሆኑም ባሻገር ሥርዓቱ ባስቀመጠው መስመርም ጭምር ነው። ለዚህም ግልጽ ማሳያ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት የሲዳማ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል ጥያቄ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ማሳለፉ ነው። እንግዲህ በህዝቦች ይሁንታ የተመሰረትኩ መንግሥት ነኝ ባዩ ኢህአዴግ ህዝቦች እራሱ ባስቀመጠው ሥርዓት መሠረት ጥያቄአቸውን ሲያቀርቡ ከራሱ የፖለቲካ  ጥቅም አንጻር ትርፍ የሚያስገኝ ካልሆነና ስጋት ይፈጥርብኛል ብሎ ካሰበ ምላሽ እንደማይሰጥ የሲዳማ ህገመንግሥታዊ የማንነት ጥያቄ መልስ ማጣት ትልቅ አገራዊ ማሳያ ነው።

የሲዳማ ህዝብ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ዕጣ ፈንታው ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር እንደሆነና የኢትዮጵያን አንድነት አጥብቆ የሚሻ ህዝብ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበረውና የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ የሆነው ፍቼ ጫምባላላ  በሚከበርበት ዕለት በሲዳማ አዛውንቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች የሚጨፈረውን ባህላዊ ጭፈራ (ቄጣላ) ይዜት ማዳማጥ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ -ሲዳማ፣  ኢትዮጵያ – ሲዳማ፣ ኢትዮጵያ- ሲዳማ፣ ሲዳማ-ኢትዮጵያ፣ የሚሉ ተያያዥና ተደጋጋሚ ቃላቶች ይደመጣሉ።

በሲዳማ መንደሮች አስተማሪዎች፣ ሀኪሞች፣ ነጋዴወችና  ነዋሪወቹ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ሲዳማ የሁሉም ሁሉም ደግሞ  የሲዳማ የሆነበት አካባቢ ሰፍሮ የሚኖር ህዝብ ነው።

የሲዳማ ህዝብ ጭቆናን ለመቀበል እጁን ሰጥቶ የማያውቅና ለመብቱ በመታገል በርካታ መስዋዕትነትን የከፈለ ህዝብ ነው። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የህወኃትን የፖለቲካ ሴራ ከመነሻው በመገንዘብ ቀደም ሲል የደርግን ሥርዓት ለመፋለም ወደ መሸገበት ሱማሊያ ዳግም ከመመለስ ይልቅ በህዝቡ መሃል ሆኖ  የሠላማዊ ትግልን ምርጫው አድርጎ  ቆይቷል። ይሁንና እንደሌሎቹ የአገር ውስጥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አናት አናቱ እየተኮረኮመ የሲዳማን ህዝብ በደል በሚገባ ለማሰማት አልቻለም። ለሲዳማ ህዝብና ሌሎች ደቡብ ተብለው ያለፍላጎታቸው በአንድ ቅርጫት ውስጥ ለታጨቁት ብሔረሰቦች በህወኃት ኢህአዴግ የተመደበው -ደኢህዴን- የእራሱ አቋም የሌለው፣ በኢህአዴግ የተያዙ አቅጣጫወችን ብቻ የሚያስፈጽም ተላላኪ ድርጅት ነው። የደህኢዴን ድክመት የሚመነጨው ከአወቃቀሩም ጭምር ሲሆን ኢህአዴግ ህወሀት በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት  ከሚያደርስበት ተጽዕኖ ጋር ተዳምሮ ኢህአዴግን ካዋቀሩ ከአራቱ ድርጅቶች ደካማ ድርጅት እንደሆነ ኢህአዴጋውያኑም ያውቃሉ።

በደኢህዴን ውስጥ የሚገኙ የደቡብ ብሔር ተወላጆችም ብሆኑ ውክልና ይዘው የመጡባቸው አካባቢያቸውንም ሆነ ህዝብ ወክለው በድርጅቱ ውስጥ መታገል የሚያስችል ወኔና ድፍረት ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም የደኢህዴን አመሠራረት ዋነኛ ፍላጎት የህዝቡን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ ሳይሆን እነ አቶ ብተው በላይ የህወኃትን ስጋት ሊቀንስ በሚችል መልኩ በጥንቃቄ ያዋቀሩት በመሆኑ አወቃቀሩ በቀላሉ ለህዝቦች መብት መከበር ለሚደረገው ትግል አመች አይደለም ። ሲዳማ የመብት ጥያቄ ሲያነሳ-ወላይታው በስጋት እንድያየው-ወላይታው የመብት  ጥያቄ ሲያነሳ – ጉራጌው እንድሁ፤ ጉራጌው አንዳች ሲያነሳ ሌላኛው በጥርጣሬ እየተመለከተ፣ እየተፈራሩ እንዲኖሩ እና ህብረቱን ባይፈልጉትም ተገድደው እንዲያስቀጥሉ ተደርገዋል ። ክልሉ ለህዝቦች ጥቅም በህግ እና ሥርዓት የተዋቀረ ሳይሆን የህዝቦችን ልዩነት ለዘላቂ የፓለቲካ ጥቅም ለማዋል በጥልቅ የህዋሀት ተንኮል  የተደራጀ ነው ።

የሲዳማን የክልል ጥያቄን መመለስ ለኢህአዴግ እንደ ተራራ የከበደውም ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል ህጋዊ ሥርዓትና መሠረት እንዲሁም ትግል ስለለለ ሳይሆን ህወሀት ኢህአዴግን ዛሬም ብሆን የኦሮሚያ ትልቅነት ስጋት ስላልለቀቀው ነው።

በደኢህዴን የሚገኙ የሲዳማ ተወላጅ ካድሬወችም የሲዳማን ድምጽ ለማሠማትና በድርጅቱ እንዲተገበር የማይታገሉበት ምክንያት የደኢህዴን አባላት ስለወከሉት ብሔረሰብ ማውራት በጠባብነት ስለሚያስፈርጃቸውና የያዙትን ጊዜያዊ የስልጣን ጥቅም ስለሚያሳጣቸው ከህዝቡ ጋር ከመሰለፍ ይልቅ በስጋት ተሸብበው ሆዳቸውን ማጥገብ ስለሚፈልጉ ነው። እነ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ለማ መገርሳና ሌሎች የኦህዴድ አባላት ዘግይተውም ቢሆን ህዝባቸውን በማዳመጥ ኦሮሞ ተጎድቶአል፣ ሊደመጥ ይገባል ብለው የክልሉን ብቻ  ሳይሆን የኢትዮጵያን ፖለቲካም ጭምር የመቀየር መንገድ የተያያዙት ህዝባችንን (ኦሮሞን) ወክለናል የሚል እምነት ስለያዙ ነው።

የደቡብ ታሪክ ግን ከዚህ ይለያል። ማንኛውም የክልል የደኢህዴን  አመራር ወላይታን እንደወከለ መናገር አይችልም።  የሲዳማው የክልል ደኢህዴን አመራርም በተመሳሳይ የሲዳማን ጥቅም በደኢህዴን ማዕቀፍ አስጠብቃለሁ ብሎ  ለሲዳማ ህዝብ መከራከር አይችልም። ደኢህዴን ለደቡብ ህዝቦች አለቃ ሲሆን ለብሔረሰቦች ደግሞ በዞን ደረጃ እንዲዋቀሩ ተደርጎ ትናንሽ ደኢህዴኖች በአለቃነት ተመድቦላቸዋል። በመጠኑም ቢሆን ለብሔሮቹ ቆመናል የሚሉቱ እነዚህ የኃለኞቹ ናቸው። ሆኖም ሁሉም በክልላዊ ደኢህዴን መዋቅሮች የተጠረነፉ ናቸው። ለምሳሌ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪና ካቢነዎች በሲዳማ ዞን ምክር ቤት እንደሚመረጡ ይታመናል። ምክር ቤቱ ደግሞ ከህዝብ የተዋቀረ ስለመሆኑና (ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ብዙ ማንሳት ባያስፈልግም) የምክር ቤቱ አባላት ከሲዳማ አብራክ የወጡ ስለመሆናቸው ግን መጠራጠር አይቻልም። ሆኖም የሲዳማ የክልሉ ደኢህዴን ጠርናፊ ከሚያዘው ትዕዛዝ ውጭ እና ከሚሰጠው አቅጣጫ የተለየ የመወሠን ሥልጣን የለዉም።  የክልሉ ሲዳማ ስምርትና አቅጣጫ የሚመነጨው ደግሞ ከህዝቡ ፍላጎት ሳይሆን ከህወሀት ኢህአዴግ ነው። ኢህዴግን የሚያሽከረክረው ህወኃት ህልውናውን አሁን ካለው የደቡብ አወቃቀር ጋር የሚያስተሳስረው ስለሆነ ከሁሉ በላይ የሚያሳስበው የህዝቦች ድምጽና ፍላጎት ሳይሆን ስጋቱን ለመቀነስ ያስቀመጠው ስልት ነው።

በመሆኑም የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በሁለት አማራጭ መንገዶች ብቻ ነው። የመጀመርያው የሲዳማ ህዝብ በምርጫም ሆነ በሌላ መንገድ በድርጅቱ ላይ ጀርባውን በመስጠት ደቡብን በራሱ በህግ እንዲፈርስ የሚችልበት ደረጃ ላይ በማድረስ ስጋት መሆን ሲሆን ፣ሁለተኛው አማራጭ -ህወኃት- ኦሮሚያ ይውጠኛል የሚለውን አስተሳሰብ ስቀርፍ ይሆናል።

አገራችን ለዓለም ገበያ የሚታቀርበውን የቡና ምርት በቀዳሚነት የሚታገኘው ከኦሮሚያ ክልል ሲሆን በመቀጠል በመጠንም ሆን በጥራት በሁለተኛነት የሚያቀርበው የሲዳማ ህዝብ ባለፉት አሥርት ዓመታት  ማንነቱ ተቀብሮአል፤ ቋንቋው ከሥራ ተቋማት ሁሉ ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደርጎል፣ ከዞኑ መቀመጫ የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሚገኙ ት/ቤቶች መማሪያ እንዳይሆን በህግ ታግዶአል ። ስለ ክልል አንድነት የሚዶሰኩሩ ደኢህደኖች የደቡብ ህዝብ ቢያንስ በሚኖርበት አካባቢ  የሚነገረውን ቋንቋ እንኳን በማወቅ ማህበራዊ መስተጋብሩን እንዲያሳልጥ እድል አልሰጡትም ። በተለይም ከሀዋሳ ከተማ -ሲዳማ- የሚለውን ቃል ለማጥፋት ቀን እና ለሊት እንዲተጉ ተነግሮአቸዋል። ለዚህም በድርጅቱ የተከናወኑ ሥራወች በርካታ ሲሆኑ ወደ ዝርዘሩ በሌላ ጽሁፍ እንመለስበታለን ። በማሳያነት ግን ማንም ሰው ወደ ዞኑ መቀመጫ ሀዋሳ ጎራ ብሎ የዞን መምሪያ ህንጻዎችን መመልከት ይችላል ። አብዛኞቹ ከወረዳ ጽህፈት ቤቶች በዲዛይንም በይዞታም የሚያንሱ ናቸው። በማንኛውም ሰዓት ለማፍረስ በማያሳሳ መልኩ የተሠሩ ናቸው ። ሁሉንም የዞን መምሪያዎች በአንድ ግቢ ውስጥ ለማሰባሰብም እንቅስቃሴወች እይተደረጉ ይገኛሉ ። አንዳች ወቅት ላይ ጊቢውን በአንድ ጊዜ መዝጋቱ ቀላል ስለሚሆንና በሲዳማ ስም የተቋቋሙ ተቋማት የራሳቸው ይዞታ እንዳይኖራቸው ማድርግ ማንነትን የማጥፋት እስትራቴጅ አካል ተደረጎ ተወስዶአል። በሩቅ አላሚዎቹ የ1994 የከተማዋ ፕላነሮች መሠረት በሀዋሳ ቋሚ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የወደፊት የሲዳማ ቅርስ ህንጻዎች ጭምር እንዳይኖሩ የቅርብ ክትትል ይደረጋል ።

በትምህርት እና በዕውቅት የተካኑ የሲዳማ ልማት ማህበር ሠራተኞች በሲዳማ ዞን የጀመሩትን የልማት አብዮት በመንግሥታዊ መመሪያ እንዲያቆሙ መደርጉ ዛሬም በሲዳማ ምሁራን እና አጠቃላይ ህዝብ በቁጭት ይነሳል። የልማት ማህበሩ በአገሪቱ ከሚገኙ የልማት ማህበራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተሸላሚ የሆነ የዞን ማይክሮ ፋይናንስ ያቋቋመ፣ የራሱ ኮሌጅ (ፉራ ኮሌጅ) እና ሌሎች ትርፋማ ተቋማትን በማቋቋም ለሲዳማ ህዝብ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከመንግስት በተሻለ ማቅረብ የጀመረ ተቋም ያሳሰባቸው አካላት የማህበሩ አካሄድ የሲዳማን ቅርሶች በሀዋሳም ሆነ በሌሎች አከባቢዎች በማድረግ ህዝቡን በኢኮኖሚ፣ በባህል እና  ፓለቲካ ተጽኖ ፈጣሪ በማድርግ ራሱን ለማስተዳደር ያለውን ፍላጎት ያሳካል የሚል ስጋት ስለፈጠረባቸው ማህበሩን አፈራርሰውታል። በመሆኑም የሲዳማ ህዝብ ማንነቱን የተቀማ ህዝብ ሆኖ ደቡብ በሚባል የአቅጣጫ መጠሪያ ሥም በተዋቀረ ክልል ውስጥ ተወሽቆ እንዲኖር ተፈርዶበታል። ኢህአዴጋውያኑ በተላላኪው ደኢህዴን አማካኝነት ትኒሿ ኢትዮጵያ እያሉ ህዝቡን የሚያታልሉበት ደቡብ የሲዳማን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ማንነት የቀበረ አወቃቀር በመሆኑ እንዲፈርስ በማድረግ ህዝቦች በመረጡት አደረጃጀት ተደራጅተው ትልቋን ኢትዮጵያ በጋራ እንዲገነቡ ያስፈልጋል።

ከደቡብ ክልል አመሠራረት ጋር በተያያዘ ከአቶ መለስ እና አቶ ቢተው በተጨማሪ ጥቂት የህወኃት ሰወች ብቻ የሚያውቁአቸውን ሚስጥራዊ መረጃወችን ያካፈለኝ የቀድሞ የህወኃት ታጋይ፣ የአሁኑ እውነተኛ የዲሞክራሲ ናፋቂ ወዳጄ ምስጋናዬ ይድረስህ።