Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሕዝበ ውሳኔው መዘግየትና አንድምታው

በፍላተ ቦሮጄ

የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በሲዳማ ሕዝብ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ጸድቆ፤ የክልል ም/ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ተጠይቆ፣ ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያደራጅ የክልል ም/ቤቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠይቆ፣ የምርጫ ቦርዱ በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝበ ውሳኔውን ለማካሔድ አልቻልኩም እያለ እስከ ዛሬ መድረሱ ሕዝቡም፣ ጠላትም ሆነ ወዳጅ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡

ጥያቄው በሢዳማ ሕዝብ ም/ቤት ከተወሰነ ከ6 ወር በላይ ሆነ፡፡ እንደሕገ መንግስቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ ጥያቄው ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ የቀረው ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድ በቂ አይደለም ባይባልም እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ካለመኖሩ ጋር፣ እንዲሁም ሥራው ከሚጠይቀው ሰፊ ዝግጅት አንጻር ቀሪው ጊዜ እያጠረ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ታድያ ወሳኙ ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔው ለምን ዘገየ የሚል ነው፡፡ እውን የምርጫ ቦርድ እንደሚለው የቴክኒክና የቦርዱ አደረጃጀት የማስተካከል ጉዳይ ነው ወይስ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው?

ጥያቄውን ከመመለስ ስለአጠቃላይ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታና በደቡብ ክልል ላይ የመሪዎቻችን አተያይ ምን ይመስላል የሚለውን እንይ፡፡ የደቡብ ክልል አፈጣጠር የሚተነትኑ ሰዎች ክልሉ የተፈጠረው በሕወሓት ልዩ ስሌት ነው ይላሉ፡፡ ሕወሓቶች ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በያዙት ሥልጣን ላይ የሚያዛልቃቸውን እቅድ ስያወጡ ሁለቱን ትላልቅ ብሔሮች (አማራና ኦሮሞ) ሥልጣናቸውን ሊቀናቀኑ የሚችሉ አደጋዎች ብለው ለይተዋል ይላሉ ተንታኞቹ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ከአማራና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ስነጻጸር ፍጹም አናሳ ነው (ያው አናሳ የሚለውን ቃል እራሳቸው ያስተዋወቁት ስለሆነ ቅር አይላቸውም ብዬ እገምታለሁ)፡፡ ከአናሳ ሕዝብ ወጥተው ትላልቅ ሕዝቦችን እየገዙ ለመቆየት ሁነኛ መላ መፍጠር ነበረባቸው፡፡ እናም፣ ሁለቱን ሕዝብ በቅርበት ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን መዋቅር መፍጠር ነበረባቸው፡፡ ኢሕአዴግ የተባለ ግንባር በመፍጠር ሁለቱን ሕዝብ የሚወክሉ ድርጅቶችን አባል አደረጉ፡፡ በወቅቱ የሌሎች ሕዝቦች ጉዳይ ፈር አልያዘም ነበር፡፡ ሕወሓቶች ሁለቱን ሕዝብ በቅርበት የሚቆጣጠሩበትን ዜዴ ቢፈጥሩም ድንገት አንድ ቀን ሁኔታዎች ቢለዋወጡ ከቁጥጥራቸው ሊወጡ እንደሚቹሉም አልጠፋቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለቱን ሕዝብ ሚዛን የሚያስት ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለው ኃይል መፈጠር እና የግንባሩ አባል መሆን ነበረበት፡፡ በተጨማሪም በግንባሩ ያልተካተቱትን ሰብስቦ የሕወሓት ሁነኛ አጋር ማድግ ሌላው ስትራቴጂ ነበር፡፡

የመጀመሪያ ስትራቴጂያቸውን ዕውን ለማድግ የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች የሚል ተረታ ተረት ፈጥረው በሽግግሩ ወቅት በአምስት ክልል ተዋቅሮ የነበረውን የደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል በመጨፍለቅ አንድ ብዙ የሕዝብ ቁጥር ያለውን ክልል (ዛሬ የደቡብ ክልል የሚባለውን) መሰረቱ፡፡ በተረታ ተረታቸው አማካኝነት በክልሉ በሚገኙ ብሔሮች ስም የተደራጁትን የተለያዩ ድጅቶች በማሰባሰብ አንድ ወጥ ንቅናቄ (ዴኢሕዴን) በመፍጠር ሁለቱን ትላልቅ ሕዝቦችን ሚዛን ማርከስ (ኒዩትራላይዝ) ማድረግ የሚችል ሕዝብና ድርጅት ፈጠሩ፡፡

ይህ ስሌት የተመሰረተው በሁለት ትላልቅ ግምቶች (አሳምፕሽንስ) ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ግምት ሁሉም የደቡብ ክልል ሕዝቦች ለሕወሓት ታማኝ ሆነው ይኖራሉ የሚል ሲሆን ይኸንኑ ለማረጋገጥ የትግል ታሪክ የለላቸውን ሕዝብ ማብቃትና የግል ሥብዕና የለላቸውን ግለሰቦች ወደ ሥልጣን ማምጣት ነበር፡፡ ሁለተኛው ግምት ሁለቱ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ በታሪክ ያላቸውን አለመተማመን ተጠቅሞ ለማራራቅ ከተሰራ በጠላትነት የሚፈላለጉ ማድረግ ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ሑለቱንም ግምት ዕውን ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን ሰርተዋል፡፡ ደግሞም ተሳክቶላቸው ነበር፡፡

እነ ቡድን-ለማ (ቲም ለማ) ይኸንን የሕወሓት ስሌት ስውል ሲያድር በደንብ እየተረዱ መጡ፡፡ ስለሆነም፣ ውጫዊ ጫና (ፕሬዠር) እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁለቱን የወያኔ አገዛዝ ምሰሶዎች ለማናጋት ዜዴ መፈለግ ተያያዙ፡፡

የመጀመሪያው ወሳኝ ዜዴ በሁለቱ ትላልቅ ብሔሮች መካከል የተፈጠረውን ጠላትነት በማስወገድ መተማመን መፍጠር ነበር፡፡ ለዚህም ተግተው ሰርተው (ሥራቸውንና ስትራቴጂያቸውን የሚናስታውሰው ስለሆነ አላሰፈርኩም) ሁለቱን ሕዝብ ማቀራረብ ቻሉ፡፡ አንዱ ምሶሶ ተናጋ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምሶሶ ለማናጋት ለሕወሓት ታማኝ ካልሆኑት የደቡብ ሕዝቦች አጋር መፍጠር ነበር፡፡ ለዚህ ሁነኛ ምርጫቸው ሊሆን የሚችለው የሲዳማ ሕዝብ ነበር (በተደጋጋሚ ከሕወሓት መራሽ መንግስት ጋር ጥል ውስጥ ይገባ ስለነበረ ሲዳማን ማመን ቀላል ነበር)፡፡ ሲዳማን እንደ ሕዝብ ከመረጡ በኋላ ትልቁ ችግር ሊሆን የሚችለው የግለሰቦች ማንነት ነበር፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሲዳማን ወክለው ሥልጣን ላይ የነበሩት የግል ሥብዕናቸው የወረደ እና ለሕወሓት ፍጹም ታማኝ በመሆን የሚኖሩ ስለነበሩ፡፡ ይሁንና፣ ከባለሥልጣናቱ አንዳንድ የሕዝብ ልጆች በሕወሓት ስህተት ተቀላቅለው ስለነበረ እነሱን መቅረብ እና ሌሎች የቻሉትን ያክል እንዲያሳምኑ ማድረግ የቲም-ለማ አካሔድ ሆነ፡፡ ተሳክቶላቸው አንዳንድ የቁርጥ ቀን ልጆችን ማግኘት ቻሉ፡፡ ሁለተኛውም የሕወሓት አገዛዝ ምሶሶ ተናጋ፡፡

ከዚህ በኋላ ቲም-ለማ ሁለት ጉዳይ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ 1ኛው ውጫዊውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተቀናጀ እንዲሆንና እንዲጧጧፍ በማድረግ ሕወሓትና የሕወሓት ተወካይ በሆነው የወቅቱ ጠ/ሚ ላይ ጫና በመፍጠር ጠ/ሚው ሥልጣን እንዲለቅ ማድረግ ሲሆን 2ኛው ጠ/ሚው ሥልጣን ስለቅ ሥልጣኑን የሚረከብ ከቲም-ለማ ማዘጋጀት፡፡

የነበረውን ሀገራዊ ሁኔታ እና የሕወሓት አገዛዝ ምሶሶ የነበሩት ሁለቱ መንገዶች መናጋታቸውን ያየው ቲም-ለማ፣ ሕወሓት መበላቷን እርግጠኛ በመሆን በምትኩ ጠ/ሚ እንዲሆን የታጩት ዶ/አብይ የሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገቡ መስራቱን ተያያዘው፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች (በተለይም በዩ ቲዩብ) በኩል የዶ/ሩን ንግግሮች በመልቀቅ ዕጩ ጠ/ሚ የሕዝብ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ፡፡ ከሕዝብ ድጋፍ በተጨማሪ ከብአዴን፣ ኦሕዴድ እና ዴኢሕዴን ለሕወሓት ታማኝ የነበሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም ለማሸነፍ ተጠቅሞበታል፡፡ ይሕን ካደረገ በኋላ ቲም-ለማ የሕወሓትን የበላይነት የማይቀበል መሆኑን በአደባባይ መግለጽ ጀመረ፡፡ በሌላ በኩል የተቃውሞ እንቅስቃሴው እንዲጠናከር እንቅስቃሴውን ከሚመሩት ጋር በቅርበት መስራት ጀመሩ፡፡

ይኸንንና መሰል ጫናዎችን መቋቋም ያልቻለው ሕወሓት ጠ/ሚውን ለመቀየር ተገደደ፡፡ በፋንታው ግን ለሕወሓት ፍጹም ታማኝ የሆነውን የሲዳማውን ባለሥልጣን ለመሾም ተግቶ ይሰራ ነበር፡፡ ሕወሓት ተስፋ አድርጎት የነበረው ሁለተኛው ምሶሶ መናጋቱን አላወቀም ነበር፡፡ ቲም-ለማ ጠንካራ የሲዳማ ካዴሬዎችን አሳምነው ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር፡፡ በምላሹ የረጅም ጊዜ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ የነበረው ክልል የመሆን ጉዳይ እንደሚያስፈጽም ቲም-ለማ ቃል ገብቶ ነበር ተብሎ ይጠረጠራል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ከቲም-ለማ ጎን የተሰለፉት የሲዳማ ካቢኔ ሌሎች የዴኢሕዴን ጓደኞቻቸውን በማሳመን ደ/ር አብይ እንዲመረጥ ያደረጉት ቅስቀሳ ተሳክቶላቸው ከ 18 የማያንስ ድምጽ ከዴኢሕዴን ለዶ/ር አብይ እንዲሔድ ተደረገ፡፡ እናም የወያኔ እቅድ ስከሽፍ የቲም-ለማ ውጥን ተሳካ፡፡

ይህን ሁሉ መንገድ አልፎ የመጣው ቲም-ለማ በደቡብ ክልል ላይ የሚኖረው እይታ ምን ይሆናል የሚለውን ስናይ ክልሉ ራሱ የተፈጠረው የኦሮሞውን ተጽዕኖ ሚዛን ለማሳት መሆኑን ቡድኑ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህ ከሆነ የደቡብ ክልል መፍረስ እንዳለበት የለማ ቡድን ያለማመንታት የሚወስነው ውሳኔ ነው፡፡ ደቡብ እንዲፈርስ የነ ዶ/ር አብይ ፍላጎት ነው፡፡

ጥያቄው ክልሉ ይፍረስ ሳይሆን እንዴት ይፍረስ የሚል ይሆናል፡፡ ያለምንም ጥርጥር ክልሉ ስፈርስ ሁከትና ትርምስ በሚፈጥር መልኩ መሆን የለበትም፡፡ ከላይ እንዳየነው ቲም-ለማ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ሁለቱን የሕወሓት አገዛዝ ምሶሶ ማናጋትና ማዳከም ችሏል፡፡ ሊዳከም ያልቻለው ሦስተኛው ምሶሶ ነው፣ ማለትም በአጋር ድርጅቶች የሚመሩ ክልሎች ጉዳይ ነው፡፡ ወያኔ ዛሬ ዛሬ ሥልጣኗን ያጣች መሆኑን ተረድታ ዋናዋን ላለማስበላት እየተፍጨረጨረች ትገኛለች፡፡ እድሜዋን እያራዘመች ያለችው የጠረፍ አካባቢ ክልሎችን (ፔሪፌሪውን) በመቆጣጠር ነው ብላ ታስባለች፡፡ ለዚህም በተለያ ክልሎች ችግሮች እንዲፈጠሩና ሀገራዊ መረጋጋት እንዳይፈጠር ሌተ-ቀን እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህ ሦስተኛው ምሶሶ ሕወሓት ያለ የለለ አቅሟን ተጠቅማ የሚትጠብቀው በመሆኑ ለለውጥ ኃይሉ ከፍተኛ ፈተና ሆኖ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የደቡብ ክልል ሌላኛው የችግር ቀጠና እንዲሆን አይፈለግም፡፡ ክልሉ አንዳች ለገር ኮሽ ሳይል መፍረስ ይኖርበታል፣ በዚህ መልኩ ለማፍረስ ደግሞ አፈራረሱ በደንብ መጠናት አለበት፡ ጥናት ደግሞ ጊዜ እንደሚፈልግ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የለውጥ ኃይሉ የደቡብ ክልል የጥናት ውጤቱ እስኪደርስ ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ ይፈልጋሉ፡

ሁለተኛው ክልሉ ባለበት እንዲቆይ የሚያስገድደው ምክንያት ደብቡ ፈርሶ የሚፈጠሩ ክልሎች ሁለት ነገሮችን መሰረት ያደረጉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ 1.ኛው፣ ልክ እንደሕወሓት ኦዲፒ አንዴ እጁ የገባው ሥልጣን ከእጁ እንዲወጣ አይፈልግም፡፡ ይህ ከሆነ የሚፈጠሩ ክልሎች የኦሮሞን ሕዝብና የሚመራውን ፓርቲ (ኦዲፒ) ጥቅም የሚያስጠብቁ እንጂ የማይጋፉ መሆን አለባቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ የሚፈጠሩት ክልሎች ጠንካራ እንዲሆኑ አይፈለግም፡፡ 2ኛው፣ የሚፈጠሩት ክልሎች ለአስተዳደር የሚያስቸግር አከላለልና የክልል ቁጥር ይዘው እንዲመጡ አይፈለግም፡፡ በሌላ አነጋገር የሚፈጠሩት ክልሎች ቁጥር ውስን ሆኖ ለጠቅላላ አስተዳደር የሚመች መሆን ይኖርበታል፡፡ እንግዲህ እነዚህ መስፈርቶች ያሟሉ ክልሎች መፈጠራቸው እስኪረጋገጥ ቅርጫቱ ክልል ባለበት እንዲቆይ የቲም-ለማ ፍላጎት ነው፡፡

የሲዳማ ፍላጎት በቲም-ለማ ዕይታ

ከአማራ ሕዝብ ጋር የተፈጠረው ጊዜያዊ ስምምነት ቀጣይ ስለመሆኑ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እርግጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡ ስለሆነም፣ ሁለተኛወን አማራጭ (ፕላን ቢ) አስቀምጠው መሔድ ይፈልጋሉ፡፡ ልክ እንደሕወሓት፣ ኦዲፒም የአማራው ድርጅት (ድርጅቶች) ተቀናቃኝ እንደሆኑ ያስቀምጣሉ፡፡ ስለሆነም፣ በሥልጣን ተቀናቃኝ የመሆን አቅሙ የቀነሰ በአንጻሩም ቢሆን ዘላቂ ሊባል የሚችል አጋር መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ በጣም አመቺ የሆነው የሲዳማ ሕዝብ ነው (ካለው የሥነልቦናና የባሕልና የቋንቋ መቀራረብ፣ የተሻለ የሕዝብ ቁጥር (በጣም ያልበዛ፣ ያላነሰ)፣ በሀገሪቱ ፖለቲካ ጉልህ ሚና መጫወት የሚችል፣ ስጋት ያልሆነ ጠቃሚ አጋር ሊሆን የሚችል ሕዝብ ነው ብለው ስለሚያምኑ፡፡ አንደኛ ምርጫቸው ሊሆን የሚችል የሶማሌ ሕዝብ እስካሁን ከሕወሓት ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆን ባለመቻሉም ጭምር)፡፡

ስለሆነም፣ ሲዳማ የራሱን ክልል መስርቶ በሀገሪቱ ፖለቲካ ጸጽዕኖው የጎላ እንዲሆን ቲም-ለማ ይፈልጋል፡፡ ይህ ግን ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ዛሬ ላይ እንዲሆን የሚፈልጉት አይደለም፡፡ ሲዳማ ክልል እንዲሆን ቢፈልጉም፣ የሲዳማ ክልል እንዲመሰረት የሚፈልጉት ግን የሌሎቹ ጉዳይ በጥናት ከተመለሰ በኋላ እንዲሆን አጥብቀው ይሻሉ፡፡ በግልጽ ቋንቋ የሲዳማ ክልል ጥያቄ መዘግየት አለበት፡፡

መጀመሪያ ብዙ ስሌቶች መሰራት አለበት፡፡ ደቡብ ተበትኖ ሲዳማ ክልል ሲሆን አጠቃላይ የቀጠናው ሰላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ላይ ችግር በማይፈጥር መልኩ፣ የሚመሰረተው የሲዳማ ክልል በጣም ተጠናክሮ ኦዲፒ ሥልጣን ላይ ችግር በማይፈጥር፣ እንዲሁም፣ የሲዳማ ክልል መሆን በአስተዳደር ምቹነት (ፊዚብሊቲ) ላይ ችግር እንደማይፈጥር መረጋገጥ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥናት ያስፈልጋል፣ እየተጠናም ነው፤ እና ጥናቱ እስኪጠናቀቅ ክልል ብሎ ነገር አይኖርም፡ ይህ ነው የመሪዎቻችን ፍላጎት፡፡

በመጨረሻም ጥናቱ ሲጠናቀቅ ሲዳማ እንደጠየቀው የራሱን ክልል (ኢንዲፐንዴንት ስቴት) እንዲመሰርት ሊፈቀድ ይችላል፣ ካልሆነም ሌሎች ብሔሮች (ለምሳሌ ጌዴኦ፣ ቡርጂ፣ ሀላባ...) ተጨምሮ አንድ ክልል እንዲሆኑ ሊወሰን ይችላል፡፡ ይህ እንግዲህ የሚወሰነው ከጥናቱ በኋላ ይሆናል፡፡ በአጭሩ የሲዳማ ክልል ሕዝበ ውሳኔው የዘገየው በምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ እንደተነገረን በቴክኒካል ምክንያቶች አይደለም፡፡ በፖለቲካዊ ውሳኔ ነው እንጂ፡፡

ይህ ከሆነ የሰሞኑ የመግለጫ ጋጋታ ምንድነው?

ሰሞኑን በነበረው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ አብይ ቀደም ብለው በመምህራን ስብሰባ ላይ የተናገሩትን በሚቃረን መልኩ የሲዳማ ክልል ጥያቄ ማንም ቢሆን የሚቀለብሰው አይደለም ብለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ከቀናት በኋላም የድንበርና የማንነት ኮሚሽን አባላት በሰጡት መግለጫ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ያለቀለት በመሆኑ በኮሚሽኑ የሚታይ አይደለም የሚል መግለጫ ሰተዋል አሉ (በርግጥ መግለጫውን አልተከታተልኩም)፡፡

ታዲያ ይህን ሁሉ መግለጫ መስጠት ለምን አስፈለገ; ጉዳዩ ያለቀለት ከሆነስ ለምን ሕዝበ ውሳኔውን አላደራጁም; ለምንስ ጠ/ሚንስቴሩ በመምህራን ስብሰባ የተናገሩትን የሚቃረን ኃሳብ ተናገሩ; እነዚህ ጥያቄዎች በጥሞና መመለስ ያለባቸው ናቸው፡፡

እኔ እነደሚገምተው ግን እነዚህ መግለጫዎች ማዘናጊያ ናቸው፡፡ ክቡር ጠ/ሚው በመምህራን ስብሰባ ላይ ያወሩት በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር፡፡ ያንን ተከትሎ ሕዝበ ውሳኔው ይደረግልን የሚል ጥያቄም ገፍቶ መጥቶ ነበር፡፡ ጥያቄው በወቅቱ ምላሽ ካላገኘ ደግሞ በክልሉ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ከላይ እንዳስቀመጥኩት አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ በክልሉ የጎላ ችግር እንዲፈጠር አይፈለግም፡፡ ስለሆነም፣ ሕዝቡን የሚያረጋጋና የሚያዘናጋ ነገር ማድረግ ነበረባቸው፡፡ እናም ጥያቄህ ማንም የምይቀለብሰው ነውና ተረጋጋ ለማለት ነበር፡፡

ከዚያስ?

ከዚያማ እንደምንም እያረሳሱ የአንድ ዓመት ጊዜው እንዲያልቅ ማድረግ ነው ዕቅዱ፤፤ የአንድ ዓመት ጊዜው ስያልቅ ኢ-ሕገመንግስታዊ አንቀጽ በሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ጉዳዩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በይግባኝ እንዲቀርብ ለማድረግ ይመስላል አካሔዱ፡፡ በአዋጁ መሰረት ይግባኝ የቀረበበት ምክር ቤት (የፌዴሬሽን) በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል ይላሉ፡፡ እናም፣ በዚህ ሥነ-ሥርዓት አማካኝነት መሪዎቻችን ሁለት የእፎይታ ዓመታት ያገኛሉ ማለት ነው፡፡

የሁለት ዓመት ጊዜው እስኪያልቅ ከላይ የተጠቀሰው ጥናት ይጠናቀቃል፡፡ የጥናት ውጤቱም ለሲዳማ ለብቻው ክልል መስጠት ወይም ከሌሎች ጋር ማቆራኘት ሊሆን ይችላል፡፡

እንግዲህ ጠቅለል ሳደርገው መሪዎቻችን የሲዳማን ክልል ልሁን ጥያቄ ባይቃወሙም አሁን እነዲመለስ አይፈልጉም፡፡ ጊዜ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ጊዜ እንዲሰጣቸው (እንዲኖራቸው) ክቡር ጠ/ሚ በተደጋጋሚ ሞክረዋል፣ አልተሳካም (በመጀመሪያ ስብሰባቸው ከሞቴዎቻችሁ ጋር ተማከሩ ያለው፣ የዞን ምክር ቤት ለውሳኔ በተጠራበት ቀን አስቸኳይ ስብሰባ አዲስ አበባ መጠራቱ፣ በቅርቡ በመምህራን ስብሰባ ላይ የተናገሩት... ያንን ያሳያል)፡፡ ስለሆነም፣ በተጠና አካሔድ ጥያቄው እንዲዘገይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝበ ውሳኔው እንዳይካሔድ ሰበብ በመፍጠር ማዘግየትና ሕጋዊ ሽፋን ያለው በማስመሰል ማዘግየት፡፡

ታዲያ ከሲዳማ ሕዝብ፣ ከፖለቲከኞቻችንና ከኤጄቶ ምን ይጠበቃል?

ፖለቲከኞቻችን ከኦህዴድ (ከቲም ለማ) ጎን ስቆሙ የተሰጣቸውን ተስፋ በማመን የተዘናጉ ይመስላሉ፡፡ ወዳጄ፣ በፖለቲካው ዓለም ቋሚ ወዳጅም ሆነ ቋሚ ጠላት እንደለለ፣ ቋሚ የጥቅም ግንኙነት ብቻ እንደሚኖር ለናንተ መናገር ያለብኝ አይመስለንም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኦዲፒ የሚያሰላው ዘላቂ ጥቅሙን እንዴት እነደሚያስጠብቅ እንጂ የሲዳማን ወይም የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ስለማስከበር አይደለም፡፡ ይኸንን የሚያደርገው የራሱ ጥቅም የተጠበቀ መሆኑን ሲያረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ፖለቲከኞቻችን የሲዳማን ሕዝብ ለቀጣይ እንቅስቃሴ ስትራቴጂ ነድፈው ማዘጋጀትና መምራት ይኖራቸዋል፡፡

ነጻነትን ትወስዳለህ እንጂ የሚሰጥህ የለም፡፡ ነጻነትን ለመውሰድ (ነጻ ለመሆን) አስፈላጊውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይኖርብሃል፡፡ መሪዎች ሁሌም ቢሆን የራሳቸውን ሥልጣን ሲያደላድሉ ብቻ ነው ሕዝብን የሚያስታውሱት፡፡ ሕዝብ እራሱ እንዲያስታውሱት ካላስገደዳቸው፡፡ ስለዚህ፣ የሲዳማ ሕዝብ፣ በተለይም ኤጄቶ ያለውን ሰላማዊ የትግል ስልት በሙሉ ተጠቅሞ ሕዝበ ውሳኔው እንዲፈጥን ማድረግ ይኖርበታል፡፡

በተያዘለት ጊዜ ሕዝበ ውሳኔው የማይካሔድ ከሆነ ግን በሕገ መንግስቱ መሰረት መብታችንን ለማወጅ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ መብታችሁን ለምኑ የሚለውን የአዋጁን አንቀጽ ኢ-ሕገ መንግስታዊ ስለሆነ እንደለለ በመቁጠር (ለነገሩ የአዋጅን ኢ-ሕገ መንግስታዊነት መወሰን በኛ አልተጀመረ)፡፡

ለማኝኛውም፤ ስለሕዝበ ውሳኔ መፍጠንና ቀጣይ የትግል አቅጣጫ በተመለከተ ኤጄቶ ለነገ ማለትም ጥር 20/2011 ጣት ሶስት ሰዓት ላይ አጠቃላይ ስብሰባ ጠርቷል፡፡