Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ጊዜ ያለፈበት እሳቤ - “እናውቅልሃለን”

ዶ/ር ሽፈራው ሙለታ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ)

እንደመነሻ፡ “ወርቃማው ዘመን ከበስተጀርባችን ያለው (ያለፍነው) አይደለም፡፡ ከፊት ለፊታችን የሚገኘው ነው፡፡ ወርቃማው ዘመን የማሕበራዊ ሥርዓት ተጠናቆ መፈፀም ማስረጃ ነው፡፡ አባቶቻችን አላዩትም፡፡ ልጆቻችን አንድ ቀን ይደርሱበታል፡፡ የእኛ ሚና መንገዱን መጥረግ (ማሳመር) ነው፡፡” ሴን ትሲሞን /Saint Simon/ 
ይህ የፈረንሳዊው ፈላስፋና እና ፖለቲከኛ የሳን ሲሞን (1760- 1825 እ.ኤ.አ የኖረ) አባባል፤ በበርካታ ልሂቃን በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የሰው ልጆችን ሕይወት የተቃና ለማድረግ “የማሕበራዊ ሥርዓት” መደላድልን ማበጀት እጅጉን ወሳኝ መሆኑን ስለ ሚያመለክት ነው፡፡ ይህን የማህበራዊ ሥርዓት መደላድል ግን በእኛ ሀገር በሚገባ መዘርጋት አልተቻለም፡፡

ለዚህ ሁኔታ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ የዘለቀው በየዘመናቱ የሚመጡና የሚሄዱ ገዢዎች ለሕዝባቸው “እኛ እናውቅልሃለን” ባይ መሆናቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከሕዝባቸው ፈቃድና ይሁንታ ውጪ የራሳቸውን ብቻ እየጫኑ የኃይል አገዛዝን በማስፈናቸው አያቶቻችን የተደላደለ ማሕበራዊ ሥርዓት ሳያዩ ማለፋቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በአጭሩ “በእኛ እናውቅልሃለን” ባዮች ሕዝባችን በሚፈልገው መንገድ መተዳደርና መኖር አልቻለም፡፡ ጊዜ ያለፈበት እሳቤ - “እናውቅልሃለን” ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝም ጊዜው ባለፈበት በዚሁ እሳቤ ላይ የተንተራሰ ፅሁፍ በ“ፍትሕ” መፅሄት፣ አንደኛ ዓመት ቁጥር 8 ታሕሳስ 2011 ዓ.ም ዕትም ለንባብ መብቃቱ ነው፡፡

በዚህ ዕትም አቶ 'ቻላቸው ታደሰ' የተባሉ ግለሰብ “ኦሮማይ ሲዳማ! - ኦሮማይ ሃዋሳ!” በሚል ርዕስ ዘለግ ያለ፤ ነገር ግን በማር የተለወሱ ቅጥፈቶችና ውሸቶች የታጨቁበት ፅሁፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ አቶ ቻላቸው ታደሰ በፅሁፋቸው የሲዳማ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመስረት ጥያቄ ካቀረበ ጀምሮ በዚሁ ጉዳይ በተደጋጋሚ እየፃፉ ነው፡፡ ለነገሩ በፈለጉት ጉዳይ ላይ የመፃፍ/ሃሳብ የመሰንዘር መብት አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሃሳብን በመግለፅ ሽፋን የተዛቡና በማር የተለወሱ ውሸቶችን ለማስተላለፍ መትጋታቸው አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ስለዚህም ነው በአቶ ቻላቸው የተዛቡ መልዕክቶች ላይ ጥቂት ነገር ለማለት የወደድኩት፡፡

አቶ ቻላቸው በዚህ ፅሁፍ ለማስተላለፍ የፈለጉት መልዕክት በሶስት ዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ ማጠቃላል ይቻላል፡፡ እነሱም፤ ሲዳማ ክልል ከሆነ፣ በሲዳማ እና በሌሎች መሃከል የ”እኛ/እናንተ” ትርክት ይሰፍናል፤ ይህም ትርክት ሌሎችን “መጤ/ሰፋሪ” የሚል እና ሌሎችን የሚያገል እንደሚሆን፤ ሲዳማ ክልል ከሆነ፣ ከአጎራባቾቹ ጋር ግጭት ውስጥ እንደሚገባ፤ የሲዳማ ብሔርተኝነት “የታሪክ እርማት” እየተደረገበትና እየተፋለሰ እንደሆነ፤ ወዘ.ተ የሚል ነው ዋነኛ ይዘቱ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሲዳማን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ “ቅዠት” የሚመስል ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ የሲዳማ ወጣቶችን፣ “ኤጄቶዎችን” ጭራቅ አድርጎ ለመሳል ሞክረዋል፡፡ የሲዳማ ብሔርተኞችንም “የብሔረሰብ ኢንተርፕነርነሮች” አድርገው በማቅረብ የተሳሳተ መረጃ አስተላልፈዋል፡፡ እኔም በእነዚሁ ነጥቦች ላይ ነው ሃሳቤን በቅደም ተከተል መግለፅ የምፈልገው፡፡

ፀሐፊው ከላይ የጠቀስነውን የተዛቡ መልዕክቶች ቢያስተላልፉም፣ እየመረራቸውም ቢሆን የሲዳማን ክልል የመሆን አይቀሬነት የተቀበሉ ይመስላሉ፡፡ ይሁን እንጂ “ተግባራዊ አዋጪነቱን” ያጠይቃሉ፡፡ ይህ መሰሉ ጥያቄ ለእኔ ለረዥም ዘመን የቆየው እና ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተደደር አይችሉም የሚለው ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብ ነፀብራቅ ነው፡፡ ራሳቸውንም ከዚህ መሰልPrejudice ቢያፀዱ ነበር የሚሻለው፡፡ ውጤቱን ወደፊት የምናየው ነውና፡፡ በፅሁፋቸው የሲዳማ ሕዝብ ሌላውን አግላይ እንደሆነ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ ይህ የሲዳማ ሕዝብ ሁሉን አቃፊነት (inclusive) ካለማወቅ የመጣ አይመስለኝም፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሲዳማ ውስጥ የኖሩ ናቸውና፡፡ ከእሳቸው የንባብ ተመክሮ አንፃርም እውነታው ይጠፋቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡ በሌላ አነጋገር ከግለሰብ ጋር ያለባቸውን ቁርሾ መነሻ በማድረግ ሲዳማን አግላይ አድርገው ማቅረብ ስለፈለጉ እንጂ ሐቁ ጠፍቷቸው ነው ብዬ አልገምትም፡፡

የሆነ ሆኖ የሲዳማን ሁሉን አቃፊነት ሐቅ በውስጡ ተወልደን ካደግን እና ከምንኖር የሚሰወር አይደለም፡፡ ይህንን በከተሞች ያለውን አብሮ የመኖር ሁኔታ ሁሉም የሚመሰክረውን ይቅርና፣ በገጠር ስላለው ሁኔታ በምሳሌ ላስረዳ፡፡ ሀ) እኔ ተወልጄ ካደግኩበት አፖስቶ ቀበሌ በጥቂት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የገጠር መንደር (ሂዳ ገጠር ቀበሌ) በርካታ የወላይታ ብሔረሰብ አባላት ይገኛሉ፤ እነኚህ የወላይታ ብሔረሰብ አባላት በሸክላ ስራ ነው የሚደተዳደሩት፡፡የሲዳማ ህዝብ በሰጣቸው የገጠር መሬት ላይ ለረጅም ጊዜያት ከሲዳማ ጋር አብረው ኖረዋል፣ እየኖሩም ነው፡፡ መቼ እና እንዴት እንደመጡ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡ በሌሎች የሲዳማ አካባቢዎችም ከ200 ሺህ እስከ 300 ሺህ የወላይታ ተወላጆች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በሲዳማ ውስጥ ሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦችም ከሲዳማ ጋር ተዋልደውና ተፈቃቅረው ይኖራሉ፡፡ ይህንን ዕውነታም በተመሳሳይ ሁኔታ በምሣሌና በመረጃ ጭምር ማሳየት ይቻላል፣ አቶ ቻላቸው ስለ ወላይታ ብቻ መዘው ስለፃፉ እንጂ፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ የሚያስፈልገው ፀሐፊው አቶ ቻላቻው እንደሚሉት ሳይሆን በሁለቱ ብሔረሰብ መሃከል አብሮ የመኖር ባህል ለዘመናት የዘለቀና የዳበረ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ወደፊትም በሁለቱ ብሔሮች መሃል ምንም ዓይነት ግጭት ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ 
እዚህ ላይ “መገመት” የሚለውን ቃል ከ“እርግጠኝነት” ጋር እንዳያምታቱት አደራ እላለሁ፡፡

ለ) በአርባ ምንጭ መምህራን ተቋም ውስጥ Dagoomu Roso (የሕብረተሰብ ትምህርት) በማስተምርበት ወቅት ከሰልጣኞቹ ግማሽ የሚሆኑት ፀሐፊው “መጤ” ብሎ የሚጠራቸው ነበሩ፡፡ ይህ የሚያሳየው በሲዳማ ዞን ውስጥ በመምህርነት ተቀጥሮ ለመሰራት የሚያስፈልገው የሰልጣኞቹ የቋንቋ ዕውቀት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “እኛ/እናንተ” የሚል ክፍፍል የለም ማለት ነው፡፡ ይህን መሰሉ የ“እኛ/እናንተ” ፍረጃ ኖሮም አያውቅም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡

ሐዋሳን በተመለከተ፡- ተጠቃሹ ፀሐፊ አቶ ቻላቸውን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች (ESAT በዋናነት) ሲዳማ ክልል ከሆነ የሐዋሳ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ያነሳሉ፡፡ ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚያቀርቡት ሐዋሳ ከተማ “የለማችው” በደቡብ ክልል ሃብት ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ውሃ የማይቋጥር ስለሆነ ብዙ ሃተታ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሐዋሳ ከተማ በራሱ የውስጥ ገቢ የሚተዳደር ነውና፡፡ ይልቁንም አቶ ቻላቸው በአንፃራዊነት ከሌሎቹ የተሻለ የመከራከሪያ ነጥብ አቅርበዋል፡፡ ይኸውም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ የሐዋሳ ከተማ ተጠሪነት ለክልሉ ም/ቤት መሆኑን ጠቁመው፣ የክልልነት ጥያቄ ሲቀርብ ግን የሐዋሳ ከተማ ም/ቤት አልተሳተፈም የሚል መከራከሪያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን መከራከሪያ ሃሳብ ያቀረቡት፣ ምናልባትም የሐዋሳ ከተማ አወቃቀርን ካለማወቅ የመነጨ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

ግልፅ ለማድረግ ያህል፤ በሲዳማ ዞን ውስጥ አስራ ዘጠኝ የምርጫ ክልሎች አሉ፡፡ የሃዋሳ የምርጫ ክልል፣ የሐዋሳ ከተማንና አጎራባች የገጠር ቀበሌዎችን የሚያካትት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አመራር የሆኑ አባላት፣ የሲዳማ ብሔረሰብ ም/ቤት አባላት ናቸው፡፡ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄን ያቀረበው ደግሞ ይህ የሲዳማ ም/ቤት ነው፡፡ ይህ ማለት የሐዋሳ ከተማ ም/ቤት አባላትም ተሳትፈውበታል ማለት ነው፡፡ በአጭር ቋንቋ ሕዝበ ውሳኔ (Referendum) ሲካሄድ በሲዳማ ውስጥ ያሉ 19ኙ የምርጫ ክልሎች (የሐዋሳ ከተማ ጨምሮ) ነዋሪዎች ይሳተፉበታል ማለት ነው፡፡ ፀሐፊው እንደሚሉት ሳይሆን ሁሉም ሕብረተሰብ ዘርና ኃይማኖት ሳይለይ ሐዋሳን ማዕከል በሚያደርገው አዲሱ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት “እኛ/እናንተ” ሳይሉ በዕኩልነት የሚኖሩበትና ልማታቸውን የሚያፋጥኑበት ይሆናል ማለት ነው፡፡

የሐዋሳ ከተማን የብሄረሰቦች ስብጥር በተመለከተ፣ አቶ ቻላቸው ሆን ብለው ከ 12 አመት በፊት የነበረ መረጃ (Data) ተጠቅመዋል፡፡ የሐዋሳ ዲሞግራፊ በጊዜ ሂደት መቀየሩ አርግጥ ነው፤ተፈጥሮአዊም ነው ምክንያቱም ከአጎራባች የሲዳማ ገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ ፍልሰት ያለ ስለሆነ፡፡ በተጨማሪም ይህ የሆነው አቶ ቻላቸው ማስረጃ ሊያቀርቡለት በማይችሉት መልኩ ሳይሆን ሲዳማ በብዛት የሚኖሩባቸው ሁለት ክፍለ ከተሞች (ታቦር እና ቱላ ክፍለ ከተማ) ወደ ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ስለተጠቃለሉ ነው፡፡ በ 2015 ከሃዋሳ ከተማ ጠቅላላ 357196 ነዋሪዎች ውስጥ፣ የሲዳማ ነዋሪዎች ቁጥር 165023 (46.2%) ነበር፤ በአሁኑ ወቅት በሃዋሳ የሲዳማ ነዋሪዎች ብዛት ከግማሽ በላይ ነው፤ ልክ ባህርዳር ላይ የአማራ ተወላጅ ወይም መቀሌ ላይ የትግራይ እንደሚበዙት ማለት ነው፡፡የሃዋሳ ከተማ ካልራቀባቸው በስተቀር የከተማው መስተዳደር የሚያወጣቸውን አመታዊ ሪፖረቶች ብቻ ማየት በቂ ነበር፤አኔም የተጠቀምኩት የ2015 ሪፖረት ስለሆነ፡፡

የሲዳማ ታሪክን በተመለከተ፡- ለምን እንደሆነ ግልፅ ባይሆንም፣ ፀሐፊው በሐዋሳ ከተማ የሚገኘውን የ ሲዳማ የነፃነት ታጋይ የነበሩት የ አቶ ወልደአማኑኤል ዱባለን ሃውልት፣ እንዲሁም በሲዳማ ባሕል አዳራሽ የቆሙትን የሲዳማ ጀግኖች መታሰቢያ ሃውልቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል እንደሚፈለግ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በ ESAT ሚዲያ በተመሳሳይ የሲዳማ ጀግኖች መታሰቢያ ሃውልቶችን የሚያንቁዋሽሽ ዶክመንተሪ ፕሮገራም መዘጋጀቱን ለሚያስታውስ ሰው፣ የአቶ ቻላቸውን አላማ መገንዘብ ይቻላል፡፡የአይዲዎሎጂ ጦርነት በሲዳማ ላይ መክፈት የከሸፈበት ስልት መሆኑን ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ እዚያው በዚያው ደግሞ “የፌዴራሉ ሰራዊት ከ17 ዓመታት በፊት በከተማው ዳርቻ ሎቄ በተባለች ቦታ የፈፀመባቸው ጅምላ ግድያ …” መኖሩን ያዋሳሉ፡፡ ይህንን የሲዳማ ሕዝብ ግድያ ጠቅሰው ሁለት መስመር እንኳ እልፍ ሳይሉ “ምናልባትም ነገ - ተነገ ወዲያ ለሎቄ ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት በማቆም ሌላ የታሪክ አሻራ ማስቀመጣቸው የሚቀር አይመስልም” በማለት የሕዝቡን ትግል ለማጣጣል የጭቃ ጅራፋቸውን ይመዛሉ፡፡

ይህ መሰሉ አጉል ነቀፋ የሲዳማን ታሪክ ሆን ብሎ ለማጠልሸት ካልሆነ በቀር ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ እንደ እውነቱ በየትኛውም ዓለም አንድ ሕዝብ ለጀግኖቹ በተለያየ መልኩ መታሰቢያ ማቆሙ ያለ፣ የነበረ፣ እና የሚኖር ተግባር ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ የሲዳማ ሕዝብ ለጀግኖቹ መታሰቢያ ቢያቆም ችግሩ ምንድነው? “እኔ አውቅልሃለሁ” ከሚል እሳቤ ካልመነጨ በቀር፡፡ መታሰቢያ ሐውልት ማቆም የለብህም፣ ወይም አይገባህም ማለት እብሪተኝነት ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ በጎ ያልሆኑ አመለካከቶች ለሕዝቦች አብሮ መኖር ዕንቅፋት የሚፈጥሩ፣ የተንኳሽነት ይዘት ያላቸው ናቸውና ባይደገም መልካም ነው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፤ ፀሐፊው ሌላም “የታሪክ ፍልሰት” ያሉትን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ በግልፅ ባይጠቅሱትም በቅርቡ የታተመው “የሲዳማ ሕዝብ ታሪክ” መፅሐፍ ይመስለኛል ነገረ-ማጠንጠኛቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ከመፅሐፉ አዘጋጆች ከአንዱ ግለሰብ ጋር ተቃርኖ እንደነበራቸው ጭምር መጥቀሳቸው ነጥባቸውን ውድቅ እንደሚያደርገባቸው አለመገንዘባቸው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ የሲዳማን ሕዝብ ታሪክ በአጠቃላይ ለማንቋሸሽ የሄዱበት ርቀት የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ በጠቀሱት መፅሐፍ ውስጥ “ሕፀፅ አለ” የሚሉ ከሆነ፣ የመፅሐፍ ዳሰሳ (Book Review) ነበር መፃፍ የሚገባቸው/ያለባቸው፡፡ ሁሉም ነገር ትክክለኛ እና ተገቢ ትችት ሊሆን የሚችለው በቦታው ነውና፡፡ እሳቸው ግን ከመፅሐፉ አንዲት ዓረፍተ ነገርን ብቻ ነቅሶ በማውጣትና ሌላ ጉዳይ ውስጥ በመደንቀር የሲዳማን ሕዝብ ታሪክ ማጠልሸት ነው የመረጡት፡፡ የአንድን ሕዝብ ታሪክ ማጠልሸት ደግሞ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ፀሐፊው (አቶ ቻላቸው) ይስቱታል ብዬ አልገምትም፡፡ ምናልባት አሁን የለውጥ ጊዜ ላይ ስለሆንን፣ ያሻኝን ነገር መፃፍ ከሚል እሳቤ በመነሳት “የአዋቂነት አጉል ድፍረት” ውስጥ ተዘፍቀውም ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን ሕዝብ ታሪክ ማንኳሰስ በማንም ሆነ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት እንደሌለው አውቀው ቆም ብለው እንዲያስቡ ልመክራቸው እወዳለሁ፡፡

የሲዳማ ምሁራንን በተመለከተ፡- ፀሐፊው ምሁራንን “የፖለቲካ ኢንተርፕነሮች” አድርገው አቅርበዋቸዋል፡፡ ይገርማል! የሲዳማ ሕዝብ የክልልነት ባለመብትነትን ለማደናቀፍ በተደጋጋሚ ከሚቀርቡ መከራከሪያዎች አንዱ ጥያቄው የሕዝቡ ሳይሆን የሲዳማ ምሁራን ብቻ ነው የሚል መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ የምልዓተ ሕዝቡን ጥያቄ የማሳነስ ሙከራ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው፡፡ ፀሐፊው (አቶ ቻላቸው) ይህንን አሳፋሪ አመለካከታቸውን ለማራገብ እንዲረዳቸው የግለሰቦችን ስብዕና ማጠልሸት (Character assassination) እንደ አንድ ስልት ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ የአንድን ክልል ፕሬዝዳንት “ቀጣፊ”፣ ሌላውን የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን “የውሸት ታሪክ ፀሐፊ” ብለው እስከ መዝለፍ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ግለ - ነቀፋ ሌላኛውን ወገን (የክልልነት ጥያቄ የማይደግፈውን ወገን) ለማስደሰትና “ጀግና” ለመባል ከመፈለግ የመነጨ ካልሆነ በቀር፤ የሲዳማን ምሁራን ለነፃነት፣ ለዕኩልነትና ለፍትህ መስፈን የሚያደርጉትን/ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያሳንሰው አይደለም፡፡ ይህንን ለማስረገጥ የሲዳማ ሕዝብ፣ ቢያንስ ቢያንስ በማህበራዊ ድረ ገፅ የክልሉ ፕሬዝዳንት የአቶ ማቴዎስን ፎቶ (profile picture) ማድረጋቸውን መመልከት ይበቃል፡፡ በዚህም የክልሉ ፕሬዝዳንት ምን ያህል ቅቡልነት እንዳላቸው መገመት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጪ በአቶ ቻላቸው ብዕር የተነቀፉት ግለሰቦች መልስ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ፀሐፊው በግል ጓደኝነት ምክንያት አገኘሁ ያሉትን “ማስረጃ” ለግል ፖለቲካዊ ፍጆታ ማዋላቸው እጅጉን አስተዛዛቢ (አሳፋሪ) መሆኑን መግለፅ እወዳለሁ፡፡

ማጠቃለያ፡- በተለያየ ቦታ፣ በተለያየ ሁኔታ የነፃነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብም ላለፉት 27 ዓመታት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄም ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በአንፃራዊ መልኩም ራስን በራስ የማስተዳደር አጋጣሚ አግኝቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ (እዚህ ላይ ኢሕአዴግ ሀገሪቷን ከመቆጣጠሩ በፊት 1981-1983 ዓ.ም “የሲዳማ አስተዳደር ክልል“ በሽግግር ወቅት “ክልል ስምንት” መባሉን ልብ ይሏል) ይሁን እንጂ በ1987 ዓ.ም ደቡብ ክልል ሲመሰረት የሲዳማ ህዝብ ያገኘውን ራስን የማስተዳደር መብቱን መልሶ አጣ፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ የሲዳማ ሕዝብ በፖለቲካ አፈና ውስጥም ሆኖ ሕገ-መንግስታዊ መብቱን ለማስከበር በፅናት መታገሉን ቀጠለ፡፡ በትግሉም ብዙ ዋጋ ከፈለ፡፡ እዚህ ላይ ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ.ም በሎቄ አቅራቢያ የተጨፈጨፉትን 70 የሲዳማ ወጣቶችን መስዋዕትነት ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡ ይህ ጭፍጨፋ ለዛሬዎቹ “ኤጀቶዎች” የቅርብ ጊዜ ትዝታም ነው፡፡ በዚህና በዚህ መሰል መስዋዕትነት ውስጥ ያለፈው የሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ትግል ዛሬ የማይቀበለስበት (Irreversible)ደረጃ ደርሷል፡፡ የሲዳማ ም/ቤት ራስን የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብትን ለመጎናፀፍ ውሣኔን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ ይህ የነፃነት፣ የእኩልነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥቃቄና ውሣኔ ደግሞ በተራ አሉባልታ አይደናቀፍም፡፡

ፀሐፊው አቶ ቻላቸውም ሆኑ ሌሎች በተጣረሰና ዘመን ባለፈበት “እኔ አውቅልሃለሁ” አባዜ የሲዳማን ሕዝብ ትግል ሊያደናቅፉት እንደማይችሎ መረዳት አለባቸው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ፣ ሐዋሳን ማዕከሉ ያደረገ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መሆኑን የሚያበስርበት ጊዜ ቅርብ ነውና፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለበርካታ ለዘመናትና አዝማናት፤ ቅመ፣ ቅድመ አያቶቻችን፣ እና አባቶቻችን በተደላደለ ማሕበራዊ ስርዓት ማለፍ አልቻሉም፡፡ ልጆቻቸውና የእኛ ልጆች ግን ካለፈቃዳቸው የሚመሰረት መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ መኖር የለባቸውም፡፡ ልጆቻችን ካለፈቃዳቸው በሚቆም የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ እንዳይኖሩ የምንሻ ከሆነ ደግሞ እኛ አንዳች ሚና (ራዕይ) ሊኖረን ይገባል፡፡ ያ ሚናችን ደግሞ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርአት ማምራት የሚያስችለውን ጥርጊያ ማሳመር መሆን አለበት፡፡ ጥርጊያውን በማሳመር ረገድ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ባለ ራዕይ መሆን አለበት፡፡ ራዕይ የሌለው ትውልድ በቁሙ እንደሞተ ይቆጠራል፡፡ ለልጆቹም የሚያወርሰው ያንኑ ሞት ነው፡፡ ይህ ወደፊትም እንዳይሆን ነው የሲዳማ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርና የክልላዊነት መብትን ዕውን ለማድረግ የታገለው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ዕውን ሲሆን ነው የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሕያውነት በፅኑ መሰረት ላይ የሚቆመው፡፡

ስለዚህ የብሔሮችን መብት በማክበር እና በማስከበር ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እንትጋ!